በእነ ውብሸት ታየና ርእዮት አለሙ ላይ የተላለፈውን ውሳኔ አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅት ተሟጋቾች እያወገዙት ነው

ጥር 19 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች መብት አስከባሪ ድርጅት በእንግሊዝኛው አጠራር ሪፖርተርስ ዊዝ አውት ቦርደርስ በእነ ውብሸት ታየና ርእዮት አለሙ ላይ የተላለፈው ውሳኔ የኢትዮጵያን ምስል የሚያበላሽ ነው።

“የኢትዮጵያን የፍትህ ስርአት መረዳት አይቻልም” ያለው ድርጅቱ ፣በ ህገመንግስቱ የተቀመጡትን መብቶች በግልጽ እንደሚጋፋ በሚነገርለት የጸረ ሽብር አዋጅ ተጠቅሞ ጋዜጠኞችን መቅጣት ተቀባይነት የሌለው ጉዳይ ነው ብሎአል።

ርእዮትና ውብሸት ወንጀለኞች ባለመሆናቸው በአስቸኳይ መፈታት አለባቸው በማለት ሪፖርተርስ ዊዝ አውት ቦርደርስ ገልጧል።

አለማቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተንከባካቢ ድርጅት ወይም ሲፒጄ የአፍሪካ ተወካይ የሆኑት ሙሀመድ ኬታ በበኩላቸው  ውሳኔው ከፍትህ ጋር ምንም የሚያያይዘው ነገር የለም፤ ይህ የፖለቲካ ውሳኔ ነው፣ ጋዜጠኞች ምንም ነገር እንዳይናገሩ ለማድረግ ታስቦ የተሰጠ ፍርድ ነው” ብለዋል።

 የአቶ መለስ ዜናዊ መንግስት በኤልያስ ክፍሌ የክስ መዝገብ በአሸባሪነት ወንጀል የከሰሳቸውን ሁለቱን ነፃ ጋዜጠኞች- ርዮት ዓለሙንና ውብሸት ታዬን በ14 ዓመት ጽኑ እስራትና በ33 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጫ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ዘሪሁን ገብረእግዚሃብሄር በ17 ዓመት ጽኑ እስራትና በ50 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት፣ ወ/ሮ ሂሩት ክፍሌን ደግሞ በ19 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲሁም ጋዜጠኛ ኤልያስ ክፍሌን በሌለበት በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት መቅጣቱን መዘገባችን ይታወሳል።

የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ምክትል ዋና አዘጋጅ የነበረው ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ ዳኞቹን ምንም ዓይነት አሳማኝ ማስረጃ ባልቀረበበት ሁኔታ ነው በእኛ ላይ የፈረዳችሁት ያላቸው ሲሆን፣  የአብዴፓ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ዘሪሁን እኔ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ከመሆኔ በቀር ምንም ዓይነት ጥፋት አልሰራሁም ሲሉ  እንባ እያነቃቸው ተናግረዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ተከሳሾችን ምንም ዓይነት ነገር እንዳይናገሩ በመከልከል ወደ ፊት ይግባኝ የማለት መብታቸው የተጠበቀ መሆኑን ለቀጣይ 5 ዓመታት ከህዝባዊ መብታቸው እንዲታገዱ መወሰኑን የገለጸ ሲሆን የተከሳሽ ቤተሰቦች በችሎት ላይ ማልቀስ በመጀመራቸው እስረኞችን ቶሎ ወደ ማረሚያ ቤት እንዲመለሱ ፍርድ ቤቱ አዟል፡፡

ከፍርድ ቤት ውጪ ሪፖርተራችን ያናገራቸው የጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ፣ የፖለቲከኛው አቶ ዘሪሁን ገብረእግዚሃብሄር፣ እና የወ/ሮ ሂሩት ክፍሌ ጠበቃ ደርበው ተመስገን እንደገለጹት ሁኔታው ከልብ አሳዝኖኛል፣ ዐቃቤ ህግ ያቀረበው የሽብርተኝነት ውንጀላ ገና በጅምር እንደነበር አድርጎ ነው ያቀረበው፤ በሕጋዊ መንገድ የተፈቀደ የጋዜጠኝነትና የፖለቲከኛነት ሥራቸውን በሰሩ እንዲህ ዓይነት ከባድ ቅጣት መቅጣት በእውነት ያሳዝናል፡፡ ደንበኞቼን አነጋግሬ ይግባኝ እጠይቃለሁ ብለዋል፡፡

የጋዜጠኛና መምህርት ርዮት ዓለሙ ጠበቃ ሞላ ዘገየ ለሪፖርተራችን በስልክ እንደገለጹት የሚገርምና የበዛ ቅጣት ነው የተፈረደባቸው፡፡ በዚህ ፍርድ እኔ አልስማማም፡፡ ይሄ በሙከራ ደረጃ ለቀረበ ክስ እንዲህ ዓይነት ፍርድ መስጠት ይደንቃል፡፡ ይሄን ያህል የጋዜጠኝነት ሥራ በተሰራ ቅጣት ማክበድ ይገርማል፡፡ ሕገመንግስቱን መሠረት አድርጌ ይግባኝ እጠይቃለሁ፡፡ በቅጣት ውሳኔውም በፍርዱም አልስማማም በማለት ገልጸዋል፡፡

የርዮት አባት ጠበቃ ዓለሙ ጎቤቦ በበኩላቸው በሕጋዊና ሕገመንግሥታዊ ሁኔታ ከሄድን ርዮት አይደለም እንዲህ ዓይነት የበዛ ፍርድ ውንጀላውንም መከላከል አይገባትም ነበር፤ እንደገናም ተከላከይ ስትባል በሚገባ ተከላክላ ተከራክራለች ነገር ግን ፍርዱ እንዲህ ሆኗል ምን ማድረግ ይቻላል ይግባኝ እንጠይቃለን በማለት ለሪፖርተራችን በሀዘን ስሜት ገልጸዋል፡፡