ታህሳስ 06 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በቅርቡ ከመንግሥት ጋር በመደራደር እና በግዴታ “አኪልዳማ‘ በተሰኘው የኢቲቪ የፕሮፓጋንዳ ዝግጅት ላይ ራሳቸውን፣ ሌሎች ሰዎችን እና ፓርቲዎችን በመውቀስ ለመንግሥት የድጋፍ ቃላቸውን የሰጡ ሰዎች ይገኙበታል የተባሉት በእነ አንዷለም አራጌ የክስ መዝገብ የሚጠሩት የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች እነማን እንደሆኑ በዝርዝር አልታወቁም።
ለምስክሮች ደኅንነት ሲባል ስማቸዉ እንዳይገለፅ የተደረገው ቁጥራቸዉ ከ30 በላይ የሆኑት የአቃቤ ህግ ምስክሮች በናዝሬት ከተማ አንድ ሆቴል ውስጥ አርፈው በዐቃቤ ሕግ፡- ብርሃኑ ወንድማገኝ፣ አንተነህ ጌታቸው፣ ቴዎድሮስ ባህሩ እና ዘረሰናይ ምስግና አመካይነት የምሥክርነት ቃል አሰጣጥ ልምምድ ሲያደርጉ እንደነበር አዲስ ነገር የመረጃ ምንጭ ገልጿል።
አዲስ ነገር በተጨማሪ አቶ ዘመኑ ሞላ እና ሌሎችም ጥቂት ከእስር ተፈቱ የተባሉት ሰዎች እስር ቤት ዉስጥ ባይሆኑም በቁም እስር ላይ መሆናቸውንና ከተለቀቁበት ጊዜ ጀምሮ በየቀኑ ለፖሊስ ሪፖርት እንደሚያደርጉ ከተጨባጭ ምንጭ ለማወቅ መቻሉን አስታዉቋል።
ዘጋቢያችን ከአዲስ አበባ ባስተላለፈው ዜና ደግሞ አቃቢ ህግ ባቀረበው የምስክሮች ዝርዝር ውስጥ በቅርቡ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ድርጅት በሰራው የፕሮፓጋንዳ ዶኩመንተሪ ፊልም ላይ መንግሥት የሚፈልገውን በመመሥከር የተባበሩትና ከእሥር የተፈቱት የመላው ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /መኢዴፓ/ ዋና ጸሐፊ አቶ ዘመኑ ሞላ፣ አርቲስት ደበበ እሸቱ እና የአንድነት ፓርቲ አመራር አባል አቶ አሳምነው ብርሃኑ እንደሚገኙበትና ሆቴል ተይዞላቸው ከፌዴራል ዐቃቤ- ሕግ ጋር የተጠና የምስክር ቃል አሰጣጥ ልምምድ ሲያደርጉ ቆይተው ማዕከላዊ መሰባሰባቸውን ገልጧል።
ዘጋቢያችን አቶ ዘመኑ ሞላ በሀሰት መሥካሪነታቸው ተጸጽተው ” ምነው አርፌ እንደጓዶቼ በጽናት በታሰርኩ፣ የአዕምሮ ሰላሜን ባገኝ ይሻለኝ ነበር፣ አካሌን ከእስር አስፈትቼ አዕምሮዬንና መንፈሴን ከማሳስር” በማለት ለቤተሰቦቻቸው ሲናገሩ መደመጣቸውን አክሎአል።
በአቶ መለስ መንግሥት በሽብርተኝነት ወንጀል ተከሰው በእሥር ላይ የሚገኙት ስምንት የፖለቲካ ፓርቲ የአመራር አባላት፣ ነፃ አሳቢ ዜጎች እና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ሀሙስ ጠዋት ያለቀጠሯቸው ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ መደረጉ ይታወቃል፡፡ ዛሬ አርብ ደግሞ የፌዴራል ዐቃቤ- ሕግ 35 ምስክሮችን እንደሚያቀርብ አሳውቋል፡፡
በእሥር ላይ የሚገኙት የአንድነት ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበርና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አንዷለም አራጌ፣ አቶ ናትናኤል መኮንን፣ አቶ ዮሐንስ ተረፈ፣ አቶ የሸዋስ ይሁንአለም፣ አቶ ክንፈሚካኤል ደበበ፣ አቶ ምትኩ ዳምጤ፣ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና አቶ አንዷለም አያሌው ከፍተኛው ፍርድ ቤት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት በከፍተኛ ጥበቃ ሥር ሆነው ነው ፍርድ ቤት የቆሙት።
የፖለቲካ እሥረኞች በድንገት ችሎት ላይ እንደሚቀርቡ መረጃ ያገኙ የእስረኞች ቤተሰቦች፣ የሥራ ባልደረቦቻቸው፣ የሀገር ውስጥና የውጭ አገራት ጋዜጠኞችና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰባት እንደ ሁልጊዜው በብዛት በመገኘታቸው በሦስተኛ ወንጀል ችሎት ጠባብ አዳራሽ ሊሰየም የነበረው ችሎት ወደ አንደኛ ወንጀል ችሎት ሰፊ አዳራሽ እንዲዛወር ተደርጓል፡፡
የ1ኛ 2ተኛ፣ 5ተኛ እና 7ተኛ ተከሳሾች ጠበቃ አቶ ደርበው ተመስገን የቀጠሮው መሰበር እና ችሎቱ መሰየሙ ዱብ-ዕዳ እንደሆነባቸውና ቀደም ሲል በተያዘው ቀጠሮ አጀንዳቸውን አስተካክለው ደንበኞቻቸውን ለማናገር ገና በሚሰናዱበት ጊዜ ይህ በመፈጸሙ ለችሎቱ ዝግጁ አለመሆናቸውን በመግለጽ ፍርድ ቤቱ ጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጥ ቢጠይቁም ፣ ፍርድ ቤቱ የተከሳሾች ማረሚያ ቤት መኖርና ዐቃቤ- ሕግ ምስክሮቼን ቶሎ ማቅረብ እችላለሁ ማለቱን እንደ ምክንያት በማቅረብ አቤቱታቸውን ውድቅ አድርጎ ዛሬ አርብ ምሥክሮችን መስማት እንዲጀመር ብይን ሰጥቷል፡፡
የተከሳሽ ጠበቆች ለፍርድ ቤቱ እንዳስታወቁት ከዚህ ቀደም ባቀረቧቸው አቤቱታዎች ውሳኔ ቢያገኙም እስከ አሁን ተግባራዊ ያልተደረጉ ውሳኔዎች አሉ በማለት ካቀረቡዋቸው አቤቱታዎች መካከል፣ የፌዴራል ፖሊስ ደንበኞቼን በቁጥጥር ሥር ሲያውል ከክሱ ጋር ግንኙነት የሌላቸው ንብረቶችን ወስዶ እስከ አሁን አልመለሰም፣ እስረኞች በቤተሰብ፣ በሃይማኖት አባት፣ በጠበቆቻቸው የመጎብኘት መብት ቢኖራቸውም የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት ይሄን ሕገመንግስታዊ መብት እየጣሰ ይገኛል፣ የኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት በቅርቡ አኪልዳማ በሚል የደንበኞቼን ሥም የሚያጠፋና በፍርድ ሂደት ላይ ያለን ነገር ከፍርድ ቤት በፊት የጥፋተኝነት ውሳኔ ሰጥቶ የቀረበ ፕሮግራም በመሆኑ ፕሮግራሙን ያዘጋጀው ጋዜጠኛ እና የኢቲዮጵያ ቴሌቭዥን ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ተጠርተው መልስ እንዲሰጡበት ያቀረብኳቸው አቤቱታዎች አሁንም አልተተገበሩም የሚሉት ይገኙበታል።
ፍርድ ቤቱ የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት ተወካይን በመጥራት “ለምንድን ነው የእስረኞችን መብት የማታከብሩት፣ ይሄን ለፍርድ ቤቱ እንድታስረዱ ከአንድም ሁለት ጊዜ በደብዳቤ ጥሪ አድርገንላችሁ አልቀረባችሁም” በማለት ለአቀረቡት ጥያቄ የማረሚያ ቤቱ ተወካይ ” እኔ ደብዳቤውን አድርሻለሁ ለምን እንዳልቀረቡ ግን አላውቅም” የሚል መልስ ሰጥተዋል።
የ3ተኛ፣ 4ተኛ፣ 6ተኛ እና 8ተኛ ተከሳሽ ጠበቃ አቶ ሳሙኤል አባተ ዐቃቤ- ሕግ ባቀረበው የምስክሮች ቅጽ ላይ ዝርዝር ሃሳብ እንደሌለውና ምሥክሮችንም በሥም ባለመጥቀሱ ለመከላከል ስለሚያዳግተን እንዲሻሻል ፍርድ ቤቱን ቢጠይቁም ለምስክሮች ደህንነት በሚል ጥያቄውን ውድቅ አድርጎታል፡፡
እነ አንዷለም አራጌ ህዳር 20 ቀን በዋለው ችሎት ላይ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት መብታቸውን ከመጠቀማቸው ውጪ ምንም አይነት ወንጀል እንዳልሰሩና ይልቁንም ክሱ የመንግሥት የሀሰት ድሪቶና ተረታ ተረት መሆኑን መግለፃቸው ይታወሳል፡፡