ግንቦት ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የኢህአዴግ መንግሥት የፌዴራል ዐቃቤ-ሕግ በእነአንዷለም አራጌ የክስ መዝገብ በሽብርተኝነት ወንጀል ከከሰሳቸው 24 የፖለቲካ ፓርቲ የአመራር አባላትና ጋዜጠኞች ውስጥ በሀገር ውስጥ በማረሚያ ቤት ሆነው ክሳቸውን የሚከላከሉት ስምንት ታዋቂ ኢትዮጵያዊያን ለውሳኔ ዛሬ ጠዋት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ቢቀርቡም ፍርድ ቤቱ በተለዋጭ ቀጠሮ ለሰኔ 14 ቀን 2004 ዓ.ም ሰጥቶ አሰናብቷቸዋል፡፡
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና የአንድነት ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት አቶ አንዷለም አራጌ የፍርዱን ሂደት ለመታዘብ የመጡ ሰዎችን ጎንበስ ብለው አመስግነው አይዟችሁ ብለዋል፡፡
የፍርድ ሂደቱን ለመታዘብ የመጡ በርካታ የተከሳሽ ቤተሰቦች፣ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ፣ የኤምባሲዎች ተወካዮች፣ የመብት ተሟጋቾች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች፣ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ጋዜጠኞች ቦታ የለም ተብለው መግባት ሳይችሉ ቀርተዋል፤ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደርና ጥቂት ዲፕሎማቶች ቆየት ብሎ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡
የመሐል ዳኛ እንዳሻው አዳነ፣ የቀኝ ዳኛ ሙሉጌታ ኪዳኔ እና ግራ ዳኛ ሁሴን ይመር ገና ከመሰየማቸው አቶ አንዷለም አራጌ አቤቱታ አለን በማለት ተነስተዋል።
አቶ አንዷለም “ክቡር ፍርድ ቤት እባካችሁ በርካታ ሰዎች መግባት ተከልክለው ውጪ ቆመዋል፤ የፍርድ ሂደቱን ለመታዘብ የመጡ ቤተሰቦቻችን፣ የፓርቲ ባልደረቦቻችን፣ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች፣ የኤምባሲ ተወካዮች እና ሌሎችም ከበር ቆመዋል፤ ይህ የዛሬው ቀን ለኛም ሆነ ለሀገራችን ትልቅ ጉዳይ ያለው ታሪካዊ ቀን ይመስለኛል፣ ስለዚህ ችሎቱን በሰፊው አዳራሽ አድርጋችሁ ውስጥ ገብተው እንዲታዘቡ እንድታደርጉልን እንጠይቃለን” በማለት አቤቱታውን አቅርቧል፡፡
ዳኞቹ ግራ ቀኝ ከተነጋገሩ በሁዋላ የመሐል ዳኛው ” እርግጥ ነው መዝገባችሁ ዛሬ ለውሳኔ ነበር የተቀጠረው፣ ነገር ግን መጋቢት 18 እና 19 ቀን 2004 ዓ.ም የተሰጠው የምስክሮች ቃል ከድምጽ ሪከርዲንግ ወደ ጽሑፍ ተገልብጦ ተሟልቶ ያልቀረበ የምሥክሮች ቃል ስላለ እና ተገልብጠው የቀረቡልንም ቢሆኑ በቅርቡ ደረሰን በመሆኑ አገናዝበን በቀጠሮው መሠረት ውሳኔ ለመስጠት ስላልቻልንና ዛሬ ውሳኔ ስለማይሰጥ አቤቱታችሁ ውድቅ ተደርጓል” ብለዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ለመስጠት ለሰኔ 14 ቀን 2004 ዓ.ም ተለዋጭ ጊዜ ቀጠሮ መያዙን የገለለጸ ሲሆን ፣ ስምንተኛ ተከሳሽ አቶ አንዷለም አያሌው አቤቱታ አለኝ ብሎ ሊናገር ሲል ፍርድ ቤቱ ክርክር ስላለቀ አቤቱታ አንሰማም ብሎታል። ይሁን እንጅ አቶ አንዷለም እኔ በማረሚያ ቤት በደል እየተፈጸመብኝ ነው በማለት ሲናገር ” የመሐል ዳኛው አቤቱታህን በጽሑፍ ማቅረብ ትችላለህ ብለው ገስጸውታል ። አቶ አንዷለም ግን “እስከዛሬ አቤቱታ በቃል አቅርቡ ስትሉን ስለነበረ በጽሑፍ አልተዘጋጀሁም፣ እኔ አሁን በማረሚያ ቤት የከፋ በደል እየተፈጸመብኝ ነው ይሄን ቶሎ ካላስቆማችሁልኝ …” በማለት ሲናገር ፍርድ ቤቱ ንግግሩን አስቁሞ በጽሑፍ እንዲያቀርብና የማረሚያ ቤቱን ማህተም አስደርጎ እንዲያመጣ አዞታል፡፡
የመለስ መንግስት በፈጠራ የሽብርተኝነት ወንጀል ስም በርካታ የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶችንና ጋዜጠኞችን ማሰሩ በአለማቀፍ የሰብአዊ መብቶች ድርጅት እያስተቸው ነው።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide