(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 20/2011)የባህርዳርና የአካባቢው ፍርድ ቤት በእነ አቶ በረከት ስሞዖን መዝገብ ለአቃቤ ህግ ተጨማሪ የክስ መመስረቻ ጊዜ ፈቀደ።
የዋስትና መብት እንዲፈቀድላቸው በድጋሚ የጠየቁት ተጠርጣሪዎቹ በክስ መመስረቻው ወቅት ጥያቄያቸውን እንዲያቀርቡና እስከዛው ግን በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ችሎቱ አዟል።
ችሎቱ በእነ አቶ በረከት ጉዳይም አቃቤ ህግ ህጉ በሚፈቅደው ጊዜ ውስጥ ክስ እንዲመሰርት በማዘዝ፥ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የመጠየቂያ መዝገቡን ዘግቷል።
የአማራ ክልል የፀረ ሙስና ኮሚሽን መርማሪ ቡድን በአቶ በረከት ስምንዖን እና በአቶ ታደሰ ካሳ ላይ ሲያደርግ የነበረውን ምርመራ አጠናቆ ለአቃቤ ህግ ማስረከቡን ይፋ አድርጓል።
መርማሪ ቡድኑ 613 ገጽ የኦዲት አባሪ ሰነድ፣ 35 ገጽ ሙያዊ አስተያየትና በርካታ ምስክሮችን አሰባስቦ ማጠናቀቁንና መዝገቡን ለአቃቤ ህግ ማስረከቡን ለችሎቱ በጽሁፍ አቅርቧል።
አቃቤ ህግም የተቀበለውን የምርመራ መዝገብ ተመልክቶ ክስ የመመስረቻ ተጨማሪ ቀናት እንዲፈቀድለት የባህዳርና አካባቢው ከፍተኛ ፍርድ ቤትን ጠይቋል።
ችሎቱም በዛሬ ውሎው በአቶ በረከት ስሞዖንና በአቶ ታደሰ ካሳ የምርመራ መዝገብ ላይ ለአቃቤ ህግ ተጨማሪ ቀናት የክስ መመስረቻ ጊዜ ፈቅዷል።
የወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀፅ 109 ንዑስ አንቀፅ 1 አቃቤ ህግ የምርመራ መዝገቡን በተቀበለ በ15 ቀናት ውስጥ ክስ እንዲመሰረት ይደነግጋል።
ተጠርጣሪዎች በበኩላቸው አቃቤ ህግ ከወንጀል መርማሪዎች ጋር አብሮ ሲሰራ የቆየ መሆኑን በመግለጽ ለክስ መመስረቻ ተጨማሪ ቀናት ሊፈቀድላቸው አይገባም በሚል ተከራክረዋል።
የባህር ዳርና አካባቢው ፍርድ ቤት የቤተሰቦቻችን እና የእኛን መብት እያስከበረልን አይደለም ያሉት ተጠርጣሪዎቹ፥ በክልሉ በሚገኙ ከባህር ዳር ውጭ ባሉ ፍርድ ቤቶች ጉዳያቸው እንዲታይላቸው ጠይቀዋል፡፡
አቶ በረከት ስምዖን በግል ጠበቃ የማቆም መብታቸው እንዲከበርላቸውም ለችሎቱ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡
የግራ ቀኙን ያደመጠው ፍርድ ቤቱ አቶ በረከት ጠበቃ የማቆም መብታቸው እንደሚከበርላቸው በመግለጽ ጉዳያቸው በሌላ ፍርድ ቤት እንዲታይላቸው ያቀረቡት ሀሳብ በክሱ ላይ የፍሬ ነገር ክርክር ሲጀመር የሚታይ መሆኑን ገልጿል፡፡