በአፋር ክልል ከ3 ሺ እስከ 5ሺ በሚሆኑ ታጣቂዎች ጥቃት ተፈጸመ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 20/2011) በአፋር ክልል ከ3 ሺ እስከ 5ሺ በሚሆኑ ታጣቂዎች ጥቃት መፈጸሙ ተገለጸ።

የአፋር የሰብአዊ መብቶች ድርጅት ሊቀመንበር አቶ ጋአስ አህመድ በክልሉ በተፈጸመው ጥቃት አንድ መንድር በእሳት መቃጠሉን ተናግረዋል።

ግዛትን የማስፋፋት ጥቃት ነው እየደረሰ ያለው የሚሉት አቶ ጋአስ ጥቃቱ በሶማሌ ላንድ፣በጅቡቲና በአልሻባብ ታጣቂ ሃይሎች እየተፈጸመ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ክልሉ እየደረሰበት ያለውን ጥቃት ለፌደራል መንግስቱ በተደጋጋሚ ቢያሳውቅም ምንም ያገኘው ምላሽ አለመኖሩን ነው ለኢሳት የገለጹት።

በአፋር ክልል የተከፈተው ጦርነት 3 ወራትን አስቆጥሯል ይላሉ አቶ ጋአስ አህመስ የአፋር የሰብአዊ መብቶች ድርጅት ሊቀመንበር።

ከዚህ በፊት ይካሄዱ የነበሩ ጥቃቶች ከግጦች፣ከውሃና ከሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ጋር እንደነበርም ይናገራሉ።

የአሁኑ ወረራ ግን ከዛ የተለየና ጥቃቱን የፈጸመውም አካል ቢሆን በቁጥር ከፍተኛ  ነው ብለዋል አቶ ጋአስ አህመድ ከኢሳት ጋር በነበራቸው ቆይታ። -ከ3ሺ እስከ 5ሺ በሚደርስ ታጣቂ ጥቃቱ መፈጸሙን በመግለጽ

በጥቃቱ የሶማሌ ላንድና የኢትዮጵያን ታርጋ የለጠፉ ተሽከርካሪዎች መሳተፋቸውን ነው የሚናገሩት።

እንደ አቶ ጋአስ አባባል ከሆነ ጥቃቱ ዛሬም ቀጥሏል።–በአካባቢ አንድ መንደር በእሳት መጋየቱን በመጠቆም

በአፋር ህዝብ ላይ የተከፈተው ጦርነት ኣንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይደለም ይላሉ።ጥቃቱ በጅቡቲ፣በሶማሌ ላንድና በአልሻባብ የተደረገ ጥቃት መሆኑንም ገልጸዋል።

እንደ እሳቸው አባባል አካባቢው ሰፊ ከመሆኑና የኮንትሮባንድ ንግድ የሚካሄድበት ከመሆኑም ጋር ተያይዞ የመከላከያ ሃይሉ ሁሉንም አካባቢ ለመከላከል አቅሙ የለውም።

ጥቃቱን ሊፈጽም የሚመጣው አካል የሚታጠቀው መሳሪያ ከባድ በመሆኑም የመከላከያ ሃይሉ ሊያስቆመው የሚችል አይደለም ይላሉ።

እስካሁን በተፈጸመው ጥቃትም ከ100 በላይ የሚሆኑ ወጣቶችና አርብቶ አደርጎ ህይወታቸውን አተዋል፣በቁጥር መገመት የማይቻል ንብረት ወድሟል ብለዋል።

የክልሉ መንግስት ያለውን ሁኔታ ሁሉ ለፌደራል መንግስቱ  ቢያሳውቅም የተሰጠው ምላሽ ግን እንደሌለ ነው የተናገሩት።