ነኅሴ ፳፪ (ሀያ ሁለት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጠው ኤርትራ ከሚገኘው ግንቦት ሰባት ጋር ሊቀላቀሉ ሲሉ ያዝኳቸው በሚል የሽብር ክስ የተመሰረተባቸው 1ኛ ተከሳሽ ብርሃኑ ተ/ያሬድ 2ኛ ተከሳሽ እየሩሳሌም ተስፋው 3ኛ ተከሳሽ ፍቅረማርያም አስማማው እንዲሁም 4ኛ ተከሳሽ ደሴ ካህሳይ ላይ ዛሬ ነሀሴ 22 ቀን 2007 ዓ.ም. በፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት 14ኛ ወንጀል ችሎት የአቃቤ ህግ ምስክር ተሰምቷል።
ተከሳሾቹ ‹‹አቃቤ ህግ በጻፈውና ለተከሳሽ በደረሰው የክስ ማመልከቻ ላይ አቃቤ ህግ የሰው ማስረጃ ምስክር አልጠቀሰም፤ እኛም መቃወሚያ ስናስገባም ሆነ እምነት ክህደት ቃል ስንሰጥ ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት ነው፤ በመሆኑም የአቃቤ ህግ ምስክር ሊሰማብን አይገባም›› በሚል ተቃውሞ ቢያቀርቡም ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጎታል።
ምስክሩ በሰላማዊ ትግል ወቅት ከተከሳሾቹ ጋር እንደሚተዋወቅና በ1ኛ እና 2ኛ ተከሳሽ አማካኝነት ሰላማዊ ትግሉ እንዳላዋጣ በመጥቀስ ግንቦት ሰባትን ለመቀላቀል ወደ ኤርትራ ለመጓዝ ማሰባቸውን ገልጸውለት አብርዋቸው መጓዙንና ባህርዳር ላይ ሃሳቡን መቀየሩን ተናግሯል።
‹‹ባህርዳር ላይ ለምን ለመመለስ ወሰንክ?›› የሚል መስቀለኛ ጥያቄ ከ1ኛ ተከሳሽ የቀረበለት ምስክሩ፣ ‹‹በወቅቱ ስሜታዊ የሚያደርጉ የግል ጉዳዮች ስለነበሩብኝ በስሜታዊነት የወሰንኩት ውሳኔ በመሆኑ ነው›› ሲል ተናግሯል፡፡
‹‹ለምስክርነት ያስገደደህ አካል የለም ወይ?›› ተብሎ ሲጠየቅ ‹‹የለም›› የሚል ምላሽ ሰጥቷል፡፡
‹‹ግንቦት ሰባት ነጻ አውጭ ድርጅት ነው ወይስ አሸባሪ?›› ተብሎ በተከሳሾች መስቀለኛ ጥያቄ ተጠይቆ፣ አቃቤ ሕግ ተቃውሞውን በማሰማት ‹‹ድርጅቱ በተወካዮች ም/ቤት አሸባሪ ተብሏል፡፡ ይህ የሕግ ጉዳይ ነው›› ጥያቄውን ምስክሩ የመመለስ ግዴታ እንደሌለባቸው አስረድቷል፡፡
‹‹ማዕከላዊ ታስረህ ነበር፣ ድብደባም እንደደረሰብህ በሚዲያ ሳይቀር ተዘግቧል፡፡ ልክ ነው?›› ተብሎ በመስቀለኛ ጥያቄ ሲጠየቅ ምስክሩ ‹‹ማዕከላዊ ቃል እንድሰጥ ተደርጌያለሁ፤ ግን አልታሰርኩም›› የሚል ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ የምስክሩን ቃል ከሰማ በኋላ ብይኑን ለማሰማት ለመስከረም 5 ቀን 2008 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል ሲል ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል፡፡
እነ ብርሃኑ ተክለያሬድ “የግንቦት7 አባላት ነን፣ ግንቦት7 አሸባሪ ድርጅት አይደለም፣ ግንቦት7ትን ለመቀላቀል ስንሄድ ብንያዝም ጥፋተኞች ግን አይደለንም፣ ምክንያቱም ግንቦት7 አሸባሪ ድርጅት ስላልሆነ” የሚል ጽሁፍ ጽፈው ማሰራጨታቸው ይታወሳል።