በኤፕሪል 15 የቦስተን ማራቶን ቦምብ ፍንዳታ የተጠረጠሩ ተጨማሪ ሶስት ሰዎችን ይዞ ማሰሩን የቦስተን ፖሊስ አስታወቀ

ሚያዚያ ፳፫ (ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- እንደቢቢሲ ዘገባ ፖሊስ ስለተያዙት ሰዎች ማንነትና በፍንዳታው ዙሪያ የነበራቸውን የተሳታፊነት ድርሻ በተመለከተ ተጨማሪ ነገር ከመናገር ተቆጥበዋል።

ለሦስት ሰዎች መሞትና ከ260 ሰዎች በላይ መቁሰል ምክንያት በሆነው የቦስተኑ ማራቶን የቦምብ ፍንዳታ የ19 ዓመት ወጣት የሆነው ጆሃር ሰርናዬቭ በተጠያቂነት መከሰሱ የሚታወቅ ነው። የ26 ዓመቱ የሰርናዬቨ ወንድም ከፍንዳታው 3 ቀናት በኋላ ከፖሊሶች በተተኮሰ ጥይት መገደሉ ይታወሳል።

ዛሬ ከቦስተን ፖሊስ የተሰራጨ ዜና ከፍንዳታው ጋር በተያያዘ ሦስት ተጨማሪ ተጠርጣሪዎች ተይዘዋል። ዝርዝር ጉዳዩም በማስከተል ይሠራጫል ብሏል ፖሊስ።

ባለሥልጣናት ቀደም ብሎ እንደተናገሩት በቦስተኑ የቦምብ ፍንዳታ እጃቸው ያለበት ሁለተ ወንድማማቾች ብቻ እንደሆኑ ነበር።

በጅምላ ጨራሽ መሣሪያ በመጠቀምና ዘርፈ ብዙ ውድመት በማስከተል የተከሰሰው የ19 ዓመቱ ጆሃር ሰርናዬቭ፤ በ1ኛ ደረጃ ወንጀል ከተፈደረበት የሞት ፍርድ ይጠብቀዋል።

በሆስፒታል ውስጥ ሆኖ በፖሊስ ለቀረበለት ጥያቄ መልስ የሰጠው (የ19 ዓመቱ የኮሌጅ ተማሪ) ሰርናዬቭ፤ እኔና ወንድሜ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት በኢራቅና በአፍጋኒስታን በሚያደርገው ጦርነት እንናደድ ነበር በሏል።

እንደሮይተርስ ዘገባ የሟቹን የ26 ዓመቱ ወጣት ታሜርናል አስከሬን መረከብን በተመለከተ ከቤተሰቦቹ የተደረገ ጥያቄ የለም።