(ኢሳት ዜና–ሐምሌ 12/2009) በኢትዮጵያና በኤርትራ ድንበር ኢሮብ አካባቢ በሁለቱ መንግስታት ሃይሎች መካከል የተከሰተው ግጭት መቆሙን ምንጮች ለኢሳት ገለጹ።
መጠነኛ ነበር የተባለው ግጭት የተካሄደው በሳምንቱ መጨረሻ እንደሆነ የተመለከተ ሲሆን ግጭቱን ማን ለምን አላማ እንደጀመረውም አልታወቀም
አርብ እና በተለይም ቅዳሜ ዘለግ ብሎ የቀጠለውን ግጭት በተመለከተ በሁለቱም መንግስታት በኩል የተሰጠ መግለጫ የለም።
የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ደጋፊ ድረ ገጾች ግጭቱን በተመለከተ ባቀረቡት ዘገባ ኤርትራን ተጠያቂ በማድረግ በኤርትራ ትንኮሳ የተከተለ ግጭት እንደሆነ አመልክተዋል።ብኤርትራ መንግስት በኩል ግን የተሰጠ መግልጫ የለም።
ቅዳሜ ግጭቱ በተካሄደበት ወቅት የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ 30ኛ ዙር የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ሰልጣኞችን በሳዋ በማስመረቅ ላይ እንደነበሩ ከኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ድረ ገጽ ላይ መመልከት ተችሏል።
ሆኖም ተካሄደ ስለተባለው ግጭት የተገለጸ ነገር የለም።