ግንቦት ፳ (ሀያ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በአዲስአበባና በአንዳንድ ክልሎች የማጀራት ገትር ወረርሽኝ መከሰቱንና መንግስት ጉዳዩን በከፍተኛ ምስጢር ከመያዝ ባለፈ ስርጭቱን ለመግታት ተገቢው የክትባት አገልግሎት እየሠጠ አለመሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ገለጸዋል፡፡
በማጅራት ገትር ወረርሽኝ ሰዎች እየተያዙ መሆኑንና የሞቱ ሰዎች ከየሆስፒታሉ ሪፖርት እየተደረገ ነው ያሉት ምንጮቹ ነገር ግን የኢትዮጽያ መንግስት በተለይ 50ኛውን የአፍሪካ ህብረት በዓል ያስተጓጉላል በሚል በከፍተኛ ምስጢር እንዲያዝ ማድረጉ ታውቋል፡፡
ወረርሽኑ ከተከሰተባቸው ክልሎች መካከል በጋምቤላ በአስከፊ ሁኔታ ሰዎች እያለቁ መሆኑን ምንጫችን ጠቁሞ የመንግስት ምላሽ ፈጣን አለመሆን አሳሳቢ ነው ብሎአል፡፡
በአዲስአበባ የማጅራት ገትር ክትባት ለመስጠት ታቅዶ በየጤና ጣቢያው መድሃኒቱ መሰራጨቱን ነገር ግን ከአንድ ጤና ጣቢያ መድሀኒቱ ከመሰረቁ ጋር ተያይዞ ጉዳዩ እስኪጣራ ክትባት መስጠት እንዲቆም በአዲስአበባ ጤና ቢሮ መታዘዙ ታውቋል፡፡ ክትባቱ በየት/ቤቱ ጭምር ለመስጠት ታቅዶ የነበረ ሲሆን ከመድሃኒት እጥረት ጋር ተያይዞ ዕድሜያቸው
ከ35 ዓመት በላይ የሆኑ ጎልማሶች ክትባት እንዳያገኙ ተወስኖ ለማስፈጸም እንቅስቃሴ ተጀምሮ እንደነበር ምንጫችን ጠቅሶአል፡፡
የኩፍኝ ክትባት ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች ለሆኑ ሕጻናት በአዲስአበባ ከነገ ግንቦት 21 እስከ 25 በዘመቻ ለመስጠት ፕሮግራም መያዙና ቅስቀሳ እየተደረገ ይገኛል፡፡
ወረርሽኖቹ በምን ምክንያት እንደተነሳና እንዴት መቆጣጠር እንደሚቻል በመንግስት በኩል በይፋ የተነገረ መረጃ ባለመኖሩ ዝርዝር ጉዳዮችን ለማወቅ አልተቻለም፡፡
ኢሳት ትናንት የአለማቀፍ ድርጅቶች የአወጡዋቸውን ሪፖርቶች በመያዝ የኩፍኝ በሽታ ወረርሽን መግባቱን መዘገቡ ይታወሳል።