በኢትዮጵያ የወደፊት አቅጣጫ ላይ የመከረው ስብሰባ ተጠናቀቀ

ኢሳት (መጋቢት 19 ፥ 2008)

በቪዥን ኢትዮጵያና ኢሳት በዋሽንግተን ዲሲ ጆርጅ ታውን መሪየት ሆቴል ከማርች 26-27 2016 የተዘጋጀውና በኢትዮጵያ የወደፊት ሁኔታ በለውጥ፥ ዲሞክራሲና፣ የብሄራዊ አንድነት ላይ የሚመክር ስብሰባ በስኬት መጠናቀቁን የስብሰባው አዘጋጆች ገለጹ። በስብሰባው የኢትዮጵያ የወደፊት አቅጣጫ የሚመለከቱ ጉዳዮች የተዳሰሱበት ሲሆን በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ምሁራን፣ የሲቢክ ድርጅቶች እና የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ጥናታዊ ጽሁፎቻቸውን ያቀረቡበትና የተሳተፉበት እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።

ፕሮፌሰር ጌታቸው በጋሻው የመግቢያ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ በኮንፈረንሱ አንኳር አንኳር አገራዊ ጉዳዮች እንደሚነሱ ሃሳባቸውን አንስተዋል። በኢሳትና በቪዥን ኢትዮጵያ ትብብር ተዘጋጅቶ በነበረው በዚሁ ኮንፈረንስ ከተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማት የተወከሉ ምሁራን በኢትዮጵያ ወቅታዊና የወደፊት አቅጣጫ ዙሪያም ሰፊ ውይይትን አካሄደዋል።

ከተለያዩ የሲቪክና የሰብዓዊ መብቶች እንዲሁም የእምነት ተቋማት የተወከሉ ተጋባዥ እንግዶች በኢትዮጵያ ዴሞክራሲና የተረጋጋ ሰላምን ማምጣት በሚቻልበት ዙሪያ የመከሩ ሲሆን፣ ዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያን ለመፍጠርም ብሄራዊ እርቅና ብሄራዊ ትብብር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የአፍሪካ ሃገራትን ተሞክሮ በዋቢነት በማንሳት ለታዳሚ ገለጻን ያደረጉት ፕሮፌሰር አቻምየለህ ደበላ፣ በአህጉሪቱ በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ያለው የኢህአዴግ መንግስት አይነት ምርጫ አድርጎ መቶ በመቶ አሸንፌያለሁ ብሎ ያወጀ መንግስት እንደሌለ አውስተዋል።

በጋና በናይጀሪያና በሌሎች ሃገራት በትምህርት ቆይታቸው የታዘቧቸውን ፖለቲካዊ ጉዳዮች ለኮንፈርነሱ ያካፈሉት ፕሮፌሰር አቻምየለህ፣ በሌሎች የአህጉሪቱ ሃገራት ፖለቲካዊ ለውጦች መታየት ቢጀምሩም በኢትዮጵያ ያለውን አካሄድ ግን ገና ብዙ የሚቀረው እንደሆነም አስረድተዋል።

በኒው ዮርክ ሲቲ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር የሆኑት ፕሮፌሰር ጆን ሀርብሰን በበኩላቸው, በኢትዮጵያ ከ1960 የአብዮት ፍንዳታ ጀምሮ ሃገሪቱን ዴሞክራሲያዊ ሊያደርጉ የሚችሉ አራት እድሎች ሳይሳኩ መቅረታቸውን ገልጸዋል።

በግንቦት 1977 የተካሄደው ብሄራዊ ምርጫ ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ ትግሎችን ያወሱት ፕሮፌሰር ሀርብሰን፣ ከኢትዮጵያ ጋር በሽብርተኛ ዙሪያ ትብብር ያላት አሜሪካ በሃገሪቱ ዴሞክራሲ እንዲያብብ ትብብር ማድረግ እንዳለባት ባቀረቡት ገለጻ አመልክተዋል።

የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባት የስራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት ሌንጮ ባቲ፣ በመንግስት የሚፈጸሙ የኢሰብዓዊ ድርጊቶች በዝርዝር ካስረዱ በኋላ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድነት በመሆን በስልጣን ላይ ያለውን ኢህአዴግ መስወገድ እንዳለበት ተናግረዋል።

በሃገሪቱ እየተፈጸሙ ስላሉ ኢሰብዓዊ ድርጊቶች ሰፊ ሪፖርትን ያቀረቡት አቶ ነዓምን የኢህአዴግ መንግስት ፌዴራላዊ፣ ዴሞራሲያዊ ወይም ሪፐብሊክ ተብሎ ሊፈረጅ እንደማይችል አክለው ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የወደፊት ጉዳይ የሚመክረው ስብሰባ እሁድ እለትም በዚሁ በማሪየት ሆቴል ቀጥሎ የዋለ ሲሆን፣ በትግሉና በግጭት አፈታት እና ለዲሞክራሲ፣ አንድነት ዙሪያ ሴቶች የሚጫወቱት ሚና በሚል መድረክ ውይይት ተካሄዶበታል።

በሃዋርድ ዩንቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ ተማሪ የሆነችው ወ/ሪት ኤልሳቤጥ ላቀው ወደአሜርካ የፈለሱ አፍሪካውያን ሴቶችን ጉዳይ ከኢትዮጵያውያን ትግል አንጻር ትንተና ሰጥታለች። በመቀጠልም በኖርዌይ ሃገር የሚኖሩት ወ/ሮ ሰዋሰስ ጆሃንሰን ሁሉም ኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲንና ነጻነትን በኢትዮጵያ ለማምጣት በአንድነት መታገል እንዳለባቸውና ካወሱ በኋላ፣ አዲሲቷን ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ በመጀመሪያ እርቅ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል። በመቀጠል የተናገሩት በፍራንክፈርት የሚኖሩት የሰብዓዊ መብት አቀንቃኝ ወ/ሮ አሳየሽ ታምሩ ሲሆኑ፣ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በአገር ውስጥ ለሚሰቃዩ ኢትዮጵያውያን ሴቶች አጋርነታቸውን ማሳየት እንዳለባቸው ተናግረዋል። ወ/ሮ አሳየሽ፣ “ለልጆቻችን ማውረስ ያለብን ነጻነትን ነው” ሲሉ ተደምጠዋል። በዚህ ፓነል መጨረሻ ላይ የተናገሩት በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ ሴቶች የሰብዓዊ መብት አቀንቃኝ ወ/ሮ ወሰን ደበላ ሲሆኑ፣ 51% የሚሆነውን የኢትዮጵያን የሚሸፍኑት ሴቶች ቢሆኑም፣ በአገራዊ ጉዳይ ተሳትፏቸው ግን እጅግ ዝቅተኛ ነው ብለዋል። ወ/ሮ ወሰን የኢትዮጵያ ሴቶች በአገራዊ ጉዳዮች ላይ እንዲሳተፉም ጥሪ አቅርበዋል። ፓነሊስቶቹ የኢትዮጵያ ሴቶች ድምጽ እንዲሰማ ቪዥን ኢትዮጵያና መድረኩን በማመቻቸታቸው አመስግነዋቸዋል።

እሁድ ከሰዓት በኋላ የወደፊቷን ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ለመዳሰስ ስብሰባ ተካሄዷል። ስብሰባውን የመሩት አቶ ግዛው ለገሰ ናቸው። በመጀመሪያ ጥናታዊ ጽሁፋቸውን ያቀረቡት አቶ ኤርሚያስ ለገሰ ሲሆኑ፣ በፓርቲዎችና በማህበረሰብ (ኮሚኒቲ) አባላት መካከል መተባበር አለመኖር ለለውጥ ከፍተኛ እንቅፋት እንደሆነ ተናግረዋል። ለአጭር ይሁንም ለረጅም ጊዜ የጋራ ግብ በእነዚህ የማህበረሰብ አባላትና ፓርቲዎች መካከል በመተማመን ላይ የተመሰረተ ትብብር እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል። ዶ/ር መስፍን አብዲ በመሬት ጉዳይ ዙሪያ ትንተና ሰጥተዋል። በህወሃት አገዛዝ መሬት የገበሬዎች ሆኖ እንደማያውቅና ከመሬት ይዞታ ጋር የተያያዙ አያሌ ያልተመለሱ ጥያቄዎች እንዳሉ ተናግረዋል።

አሁን ያለችዋን ኢትዮጵያ በማስመልከትም ያለፈው ታሪክ ሆኖ ያለፈ በመሆኑ የወደፊቷን ኢትዮጵያ ሁሉም በእኩል አይን የሚታይባት አገር መሆን ይኖርባታል ብለዋል። ከዚህ ጋር በማያያዝም ኦሮምኛ የኢትዮጵያ የስራ ቋንቋ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል። የኦሮሞና የአማራ ልሂቃንም በሁለቱ ህዝቦች መካከል መተማመን እንዲኖር እንዲሰሩ እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

በመሬይ ስቴት ዩንቨርስቲ የኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ሰይድ ሃሰን በመሬት ነጠቃና ሙስና ላይ ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበዋል። ፕ/ር ሰይድ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሙስና በአለም ላይ ከታዩት ሙስናዎች ለየት ያለ ነው ብለዋል። መሬት የስልጣን ምንጭ በመሆኑ የህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት መሬት ነጠቃውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተንብየዋል። ሁሉም የኢትዮጵያ ተደራሽ አካላት ይህ ዘርፈ-ብዙ ውስብስብ ችግር ለመፍታት ተቀራርበው መነጋገር እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በኬተሪንግ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ምሁር የሆኑት ፕሮፌሰር እዝቅኤል ገቢሳ፣ የዲሞክራሲ፣ የእድገት፣ የሰብዓዊ መብት፣ የሰላም ማስፈን እሴቶችን ከውስጣችን መመልከት እንዳለብን የሚተነትን ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበዋል። ኢትዮጵያ ወደ ዲሞክራሲ የምትሻገርበትን ብዙ እድሎችን ያጣችበትን አጋጣሚ የተነተኑት ፕሮፌሰር እዝቅኤል፣ ኢትዮጵያውያን ህወሃት ኢህአዴግን ከማስወገድ ባለፈ የወደፊት እቅድ ሊኖራቸው እንደሚገባ አስረድተዋል። ፕሮፌሰር እዝቅኤል በገዳ ስርዓትና በኦሮሞ እሴቶች ላይ ትንተና ሰጥተዋል።

“ከዚህ በኋላ ወዴት? ያልተመለሱ ጥያቄዎች!” የሚለው የመጨረሻው ስብሰባ የተመራው በኮሎራዶ ሜትሮፖሊታን ስቴት ዩንቨርስቲ መምህር በሆኑት በፕሮፌሰር ሚንጋ ነጋሽ ነው። ለዲሞክራሲ፣ ለለውጥና ለአንድነት ምን መደረገ እንዳለበት የመከረው ይኸው ስብሰባ፣ ኢትዮጵያ በአስቸኳይ ለውጥ የሚያስፈልጋት አገር እንደሆነች ተናግረዋል። የኢትዮጵያውያንን ህይወት የዳሰሰ በምስል ያሳዩት ፕሮፌሰር ሚንጋ፣ ኢትዮጵያ የሰላም፣ የዲሞራሲና የብልጽግና አቅጣጫ (Roadmap) ያስፈልጋታል ብለዋል። በመሆኑንም ከኤርትራ ጋር ያንዣበባት የጦርነት አደጋ፣ በኦሮሚያ፣ ኮንሶ፣ አማራ፣ ሶማሌ እና ጋምቤላ አካባቢዎች የሚታየው ግጭት ኢትዮጵያን ከፍተኛ አደጋ ውስጥ እንደከተታት ተናግረዋል። ከህወሃት/ ኢህአዴግ መወገድ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚተገበር አቅጣጫ መቀመጥም እንዳለበት ፕሮፌሰር ሚንጋ ተናግረዋል።

ፕሮፌሰር ተሾመ ከበደ በኢትዮጵያ እየተከሰተ ያለው ብጥብጥ የመንግስት የስልጣን ምንጭ እንደሆነ ለተሰብሳቢው ተናግረዋል። ፕሮፌሰር ተሾመ ኢትዮጵያ የዲሞክራሲ እሴቶችን የምታከብር፣ በሉዓላዊነቷ የማትደራደር አገር እንድትሆን ማድረግ ሃላፊነት እንዳለብን ለታዳሚው ተናግረዋል። ሕወሃት/ኢህአዴግን በተመለከተ ሙሉ በሙሉ እንዲደመሰስ ማድረግ ሳይሆን ዲሞራሲያዊ እሴቶችን እንዲቀበል ማስገደድ እንዳለብን ተናግረዋል። “አገራችን ችግር ላይ ናት፣ የእኛን እርዳታ ትሻለች” ሲሉ ለተሰብሳቢው ተናግረዋል።

ከዚህ ቀጥሎ የተናግሩት  የህግ ባለሙያና የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባት አባል የሆኑት ዶ/ር በያን አሶባ ሲሆኑ፣ ያለፉትና የአሁኑ አምባገነን መንግስታት በህዝቦቻችን ላይ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸማቸውን ተናግረዋል። ሌሎች ኢትዮጵያውያን በኦሮምያ እየተከሰተ ያለውን ህዝባዊ እንቅስቃሴ በጥርጣሬ መመከታቸውን ትተው እንዲደግፉት ጥሪ አቅርበዋል።

በካሊፎርኒያ ግዛት ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማሪያም የአምባገነን መንግስታት ባህሪ ነገሮችን መደበቅ ነው ብለዋል። በመሆኑም ህወሃት ኢህአዴግ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳይታወቅበት ኢሳትን በብዙ ሚሊዮን ብር በመክፈል በተደጋጋሚ በሞገድ ለማገድ መሞከሩን ለተሰብሳቢው ተናግረዋል። ሆኖም ህወሃቶች ለሰሩት ጥፋት ሁሉ ተጠያቂ የሚሆኑበት ጊዜ ሩቅ እንዳልሆነ ለተሰብሳቢው ገልጸዋል። ለዲሞክራሲና ለእኩልነት የሚደረገው ትግልም ህወሃት/ወያኔ ኖረም አልኖርም መቀጠሉ አይቀሬ መሆኑን አስረድተዋል። አዲስ አቅጣጫ የሚያመላክት ህገ-መንገስትም መዘጋጀት እንዳለበት ተሰብሳቢውን መክረዋል።

በመጨረሻ የቀረቡት በዳይተን ዩኒቨርስቲ የፍልስፍና መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ ናቸው። የተሻለው አቅጣጫ አሁን ያለውን በዘውግ የተከለለውን አስተዳደር መከተል መሆኑን አስመረው፣ ኢህአዴግ ቢወገድም የዘውግ ጥያቄ በቀላሉ የሚጠፋ አለመሆኑን ገምተዋል።

ከቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፎች በሁላ በርካታ ጥያቄዎች ለተሰብሳቢዎች የቀረቡ ሲሆን፣ አብዛኞቹ ከመድረክ መልስ ተሰጥቶባቸዋል። አንዳንድ ያልተመለሱ ጥያቄዎች ወደ ፊት በሚካሄዱ ስብሰባዎች እንደሚነሱ ለማወቅ ተችሏል።