በኢትዮጵያ የትራፊክ አደጋዎችን ለመከላከል በሚል የምሽት ጉዞዎች ሊከለከሉ ነው

መጋቢት ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም 

ኢሳት ዜና:-የትራንስፖርት እና መገናኛ ሚኒስቴር  የትራፊክ አደጋዎችን ለመቀነስ በምሽት የሚደረጉ  ጉዞዎችን ለማገድ ዝግጅት አጠናቅቄያለሁ አለ።

እንደ ሚኒስቴር መስሪያ  ቤቱ ገለፃ ለመንገድ የትራፊክ ደህንነት አደጋ ዋነኛ መንስኤዎች ከፍጥነት በላይ ማሽከርከር ፣ ከተፈቀደ የሰው ቁጥር በላይ መጫን ፣የመንገድ ህግና ስርአትን አለማክበር እና ህገ-ወጥ የሌሊት ጉዞ  ናቸው፡፡

ስለሆነም  በህገወጥ የሌሊት ጉዞ ተሳታፊ የሆኑ ተሽከርካሪዎችን ለመቆጣጠር በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ  የሚመራ ኮሚቴ መቋቋሙን አስታውቋል፡፡

ይሁንና በቀንም ሆነ በሌሊት የሚያሽከረክሩ ህገ-ወጥ ተጓዦችን መቆጣጠሩ ተገቢ ቢሆንም፤ አጠቃላይ የምሽት ጉዞዎችን ለመከልከል መወሰኑ ከከሚያስገኘው ጥቅም ይልቅ በህብረተሰቡ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ሚያስከትለው እንቅፋት እንደሚጎላ ከወዲሁ እየተነገረ ነው።

ከክልል ከተሞች ጋር በመቀናጀት በክልል የሚደርሱ የትራፊክ አደጋዎችን ለመቀነስና ለመከላከል የፌዴራል ፖሊሲና የትራንስፖርት ሚኒስቴር ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ገልፀዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ ከአዲስ አበባ በ200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባሉ ከተሞች አዲስ የቁጥጥር ሰርአት እንደሚጀመር አስታውቋል።

ኪሚሽኑ በሰጠው መግለጫ ሞጆ ፣ አዳማ፣ ዝዋይ፣ ሻሸመኔ ፣ ጎሀጽዮን ፣ ወሊሶ ፣ወልቂጤ፣ ደብረብርሃን፣ ደብረሲና ፣ አምቦና ነቀምቴ በዚህ ወር ቁጥጥር የሚጀመርባቸው ከተሞች እነደሆኑ ገልጿል፡፡

የአለም የጤና ደርጅት ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው በአለም ላይ በየአመቱ ከ1.3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በትራፊክ አደጋ ህይወታቸውን የሚያጡ ሲሆን፤ 90 ከመቶ የሚሆነው አደጋ የሚከሰተው ደግሞ በታዳጊ ሀገሮች ነው፡፡

ባሏት የተሽከርካሪዎች ብዛት እዚህ ግቢ የማትባለው ኢትዮጵያ ፤አስከፊና በርካታ የትራፊክ አደጋ ከሚመዘገብባቸው  የዓለም አገሮች በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች።