በኢትዮጵያ የተደነገገውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ የሰብአዊ መብት ጥሰቱ  በስፋትና በከፋ መልኩ እየቀጠለ መምጣቱን ዓለማቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ገለጸ።

ጥቅምት ፳፩ (ሃያ አንድ ) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- ሂዩማን ራይትስ ዎች  ዛሬ ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ የመብት ጥሰቱ እየከፋ መምጣቱን በመጥቀስ መንግስት አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን  ዳግም ሊያጤነውና ከዓለማቀፍ ህግጋት ጋር ተጻራሪ የሆኑ ድንጋጌዎችን  በሙሉ ሊከልሳቸው ይገባል ብሏል።

በተቃዋሚዎች  የመንግስት ህንጻዎችና የግለሰብ ንብረቶች መውደማቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስት  እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ባለፈው ጥቅምት ዘጠኝ ቀን  ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገጉን  የሰብዓዊ መብት ተቋሙ አውስቷል።

ባለፉት ጊዜያት የደህንነት ኃይሎች  በመንግስት ፖሊሲ ላይ ተቃውሞ ባነሱ  ሰልፈኞች ላይ በወሰዱት እርምጃ  ከሁለት ክልሎች ብቻ  በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውንና በአስርት ሺህዎች የሚቆጠሩ መታሰራቸውንም ሂዩማን ራይትስ ዎች ጠቅሷል።

በሂዩማን ራይትስ ዎች  የአፍሪካ ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ፌሊክስ ሆርን እንዳሉት  የኢትዮፕያ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ፤ በትንሹ ለስድስ ወራት መንግስት የማይፈልጋቸው ማናቸውም ዐይነት ንግግሮች እንዳይሰሙ እገዳ ጥሏል።

“አዋጁ ከዚህም ባሻገር ማናቸውንም ሰላማዊ እንቅስቃሴ ያፍኑ ዘንድ ለሰራዊቱ አባላት ተጨማሪ ሥልጣን ሰጥቷቸዋል” ብለዋል ፌሊክስ ሆርን። አፋኝ በሆነው አዋጅ መሰረት  በትንሹ ለስድስት ወራት ሰራዊቱ  በከተሞች ውስጥ በስፋት  የሚሰፍር ሲሆን፤ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ፣ የመደራጀት፣ የመሰብሰብና ሌሎች በዓለማቀፍ ህግጋት ገደብ የማይጣልባቸው መብቶች ሁሉ አደጋ ውስጥ ወድቀዋል።

ለእንደዚህ ያሉ የመብት ጥያቄዎች የሚሰጠው ምላሽም ወታደራዊ የኃይል እርምጃ ሆኗል። ተቃውሞው ከተጀመረ አንስቶ በደህንነት ኃይሎች እየተፈጸመ ያለውን የሰባአዊ መብት ጥሰት በመዝገብ እያሰፈረው እንደሆነ ሂዩማን ራይትስ ዎች አመልክቷል።

አዋጁ  በማህበራዊ ሚዲያዎች መረጃ መለዋወጥን፣ ከዲያስፖራ የሚተላለፉ  የቴሊቪዥን ጣቢያዎችን መከታተልን፣ እጅን ለተቃውሞ ማጣመርንና ከሚዲያዎች ጋር ግንኙነት መፍጠርን የሚከለክል ሲሆን፤በተቃዋሚዎችም እንቅስቃሴ ላይ እገዳ እንደጣለባቸው በመግለጫው ተጠቅሷል።

እንዲሁም ይኸው አዋጅ  ማናቸውንም ተቃውሞዎች ከመከልከሉም በላይ በኮማንድ ፖስት ውሳኔ ዜጎች ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ እንዲታሰሩና እንዲሰቃዩ  ይፈቅዳል ያለው ሂዩማን ራይትስ ዎች፤እነዚህ ድንጋጌዎች በተለይ ከፍተኛ ተቃውሞ በተቀሰቀሰባቸው በሁለቱ ክልሎች  በስፋት  እየተፈጸሙ መሆናቸውን ገልጿል።

የንግድ ድርጅታቸውን ለመክፈት ፈቃደኛ ያልሆኑ ሃምሳ ነጋዴዎችን ጨምሮ መንግስት  ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወዲህ 1600 ሰዎችን እንዳሰረ መግለጹን ያወሳው ሂዩማን ራይትስ ዎች፤  እስካሁን ማረጋገጥ ባይችልም  ህገ ወጥ ግድያን፣ የጅምላ እስራትንና በደህንነት ኃይሎች የሚደረግ ዝርፊያን አስመልክቶ በርካታ ሪፖርቶችን እንደተቀበለ በሪፖርቱ አትቷል። አክሎም ከመስከረም መጨረሻ አንስቶ የኢንተርኔት አገልግሎት መዘጋቱን፣ በሀገሪቱ ቀርተው ከነበሩ ጥቂት የፕሬስ ውጤቶች መካከል  አንዱ የሆነውና አዲስ ስታንዳርድ የተሰኘው  ወርሀዊ መጽሔት መዘጋቱንም አውስቷል።

በደህንነት ኃይሎችና  ማንነታቸው ባልታወቁ  ታጣቂ ቡድኖች  ግጭት መከሰቱንም ድርጅቱ ጠቅሷል። በአጠቃላይ በኦሮሚያና በአማራ ክልል  በተለያዩ ጊዜያትና ቦታ በርካቶች መገደላችውን የሰብ ዓዊ መብት ተቋሙ በዝርዝር አውስቷል።

በአሁኑ ወቅትም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስም ከዓለማቀፍ ህግጋት ጋር የማይስማሙ ድንጋጌዎች ተፈጻሚ መኾናቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቱን በማክፋት ሀገሪቱን ወደ ባሰ ቀውስ ይከታታል የሚል ስጋት እንዳላችው የገለጹት  ፌሊክስ ሆርን፤ መንግስት እርምጃውን ዳግም ያጤነው ዘንድ አሣስበዋል።