በአንድ ወር ውስጥ 248 ሰዎች መገደላቸውን የሰብአዊ መብት ሊጉ አስታወቀ

ጥቅምት ፳፩ (ሃያ አንድ ) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- አስቸኳይ የጊዜ አዋጅ ከታወጀበት እለት ጀምሮ በመላው ኢትዮጵያ የሰብዓዊ ጥሰቶች ከበፊቱ በከፋ ሁኔታ ተባብሶ መቀጠሉን በምስራቅ አፍሪካ የሰብዓዊ መብት ሊግ አስታውቋል። በተለይ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች በትግራይ ነጻ አውጪ የሚመራው የህወሃት ኢህአዴግ መንግስት ማንኛውንም የግንኙነት አማራጮችን ሙሉ ለሙሉ በመዝጋት ለዓለም ሕዝብ በማይታይ መልኩ በድብቅ በአማራ እና ኦሮሞ ብሄር ተወላጆች ላይ አሰቃቂ የጅምላ ጭፍጨፋዎችን እየፈጸመ ነው።

በምስራቅ አፍሪካ የሰብዓዊ መብት ሊግ መረጃ መሰረት በኦሮሚያ ክልል በደቡብ እና ምእራብ ኦሮሚያ እና በአርሲ ዞኖች ውስጥ 248 ሰዎች በግፍ መገደላቸውን ሲገልጽ፣ 3 ሺ 708  የሚሆኑት  ደግሞ በእስር ቤት መታጎራቸውን በሪፖርቱ ጠቅሷል። ያልተጣሩ መረጃዎች እንደሚያሳዩት  1 ሺ ሰዎች መገደላቸውን ፣ ከ40 ሺ በላይ ደግሞ መታሰራቸውን ድርጅቱ አስታውቋል።

ካለፈው ዓመት ጀምሮ እየተቀጣጠለ የመጣውን ሕዝባዊ ዓመጽን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስት በዜጎቹ ላይ የሚፈጽማቸውን ግድያዎች፣ እስራት እና የመብት ጥሰቶች  ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ጨምሮ ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ በአገርቱ የሚፈጸሙትን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በቸልታ ከማለፍ ይልቅ በድርጅቱ ሕጎች መሰረት ሊያስቆማቸው ይገባል ሲል በምስራቅ አፍሪካ የሰብዓዊ መብት ሊግ  ጥሪውን አቅርቧል።

የምስራቅ እና አፍሪካ ቀንድ የስብዓዊ መብት ጠባቂ ፕሮጀክት በበኩሉ በጋንቢያ ባደረገው 59ኛው መደበኛ ስብሰባው በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ከሚገኙት አገራት ውስጥ በተለይ በኢትዮጵያን የመብት ጥሰቶች በከፋ ሁኔታ ተባብሰው መቀጠላቸውን  ገልጿል።