ኢሳት (መጋቢት 19 ፥ 2009)
በጎንደርና በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ቤተ እስራዔላውያን ወደ እስራዔል ለማጓጓዝ የተገባው ቃል በድጋሚ መዘግየት እንዳጋጠመው ተገለጸ።
ባለፈው አመት በኢትዮጵያ ጉብኝትን ያደረጉት የእስራዔሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቤንጃሚን ኔታኒያሁ ወደ 9ሺ አካባቢ ከሚጠጉት ቤተ እስራዔላዊያን መካከል የ1ሺ 3 መቶዎቹ ጉዞ በተያዘው አመት እንደሚጠናቀቅ የተቀሩትም በአምስት አመታት ውስጥ ተጠናቀው ወደ እስራዔል እንደሚገቡ ቃል መግባታቸው ይታወሳል።
የቤተ-እስራዔላውያኑ ጉዞ ለማስፈጸም የተቋቋመው ድርጅት በመንግስት የተነበየው ቃል በመንግስት ተቋማት በኩል ባጋጠመ የቢሮክራሲ ችግር ጉዞው በተያዘለት የጊዜ ገደብ ሊካሄድ አለመቻሉን ይፋ እንዳደረገ አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ (AFP) ዘግቧል።
ጂዊሽ ኢጀንሲ የተሰኘውና የቤተ እስራዔላውያኑን ከኢትዮጵያ ለማጓጓዝ በመጠባበቅ ላይ የነበረው ይኸው ድርጅት እስካሁን ድረስ የተጓዦች ስም ዝርዝር እንኳን ከእስራዔል መንግስት እንዳልተሰጠው አስታውቋል።
ባለፈው አንድ አመት ወደ እስራዔል ይገባሉ ተብሎ ቃል ከተገባው 1ሺ 300 ተጓዦች መካከል እስካሁን ድረስ 46ቱ ብቻ ጉዞአቸው ሊሳካ የቻለ ሲሆን፣ የተቀሩት ቤተ እስራዔላውያን ጉዳዩም በድጋሚ መጓተት እንዳጋጠመው ታውቋል።
ተቋማችን ቤተ-እስራዔላውያኑ ለመቀበልና የመንግስትን መመሪያ ተግባራዊ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ቢሆንም፣ እስካሁን ድረስ የደረሰን ስም ዝርዝር እንኳን የለም ሲሉ የድርጅቱ ሃላፊ የሆኑት ይጋል ፓልመር ለዜና አውታሩ አስረድተዋል።
በእስራዔል ፓርላማ የኢሚግሬሽን ኮሚቴ ሊቀመንበር አብርሃም ንጉሴ በበኩላቸው የእስራዔል የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ሆን ብሎ ቤተ-እስራዔላውያኑ ወደ እስራዔል እንዳይጓጓዙ ብዙ እንቅፋቶችን እያስቀመጠ ነው ሲሉ ቅሬታቸውን ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ገልጸዋል። ባለፈው ወር የቤተእስራዔላውያኑን ሁኔታ ለመመልከት በጎንደርና አዲስ አበባ ጉብኝንትን ያደረጉ የእስራዔል ፓርላማ አባላት ቤተእስራዔላውያኑ እጅግ አሳዛኝ በሆነ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ከሁለት አመት በፊት ተጓዦቹን ለመውሰድ የተደረገ የበጀት እጥረት አጋጥሟል ተብሎ የቤተ-እስራዔላዉያኑ ጉዳይ እንዲዘገይ መደረጉ የሚታወስ ሲሆን፣ የቤተሰብ አባሎቻቸውን በመጠባበቅ ላይ የነበሩ በርካታ ሰዎች የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ሲያካሄዱ ቆይተዋል።
ይህንኑ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ተከትሎ በኢትዮጵያ ጉብኝትን አድርገው የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኔትናያሁ ወደ ዘጠኝ ሺ የሚሆኑንት ቤተ-እስራዔላውያን ካለፈው አመት ጀምሮ ጉዟቸው እንደሚጀምር ቃል ገብተው ነበር።
በአሁኑ ውቀት ወደ 135 ሺ የሚጠጉ ቤተ እስራዔላውያን የሚኖሩ ሲሆን 50ሺ አካባቢ የሚሆኑት በእስራዔል የተለወዱ መሆናቸው ተመልክቷል።