ህዳር 22 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በቅርቡ መንግስት አኬል ዳማ በሚል ስም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ስም ያሰራጨው የፈጠራ ድራማም፣ ጭንቀት የወለደው መሆኑን ዶክተሩ ተናግረዋል።
የህዝቡ ምሬት ከሚገባው በላይ ጨምሩአል የሚሉት ዶ/ር ነጋሶ፣ ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር መፈንዳቱ አይቀሬ ነው ብለዋል። ዶ/ር ነጋሶ እንዳሉት አኬል ዳማ ተብሎ የተሰራው ድራማ በህዝቡም ላይ ሆነ በፓርቲያቸው ላይ የፈጠረው አንዳችም ተጽእኖ ዬለም።
በሌላ በኩል ፓርቲው ህዳር 20 ቀን 2004ዓም ” በአኬልዳማ ” ድራማ የህዝብን የዲሞክራሲና የለውጥ ጥያቄ ማዳፈን አይቻልም” በሚል ርእስ ባወጣው መግለጫ “ደርግን የተካው ኢህአዴግ ትምህርት ወስዶ የተሻለ ስርዓት ይገነባል ተብሎ ቢጠበቅም፣ እሱም የለየለት አምባገነንና አፋኝ ስርዓት ለመሆን ከመብቃቱም በላይ፣ ጭቆና እንዲወገድ፣ እኩልነት እንዲረጋገጥና እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲመሠረት በሚድረግ ጥረት ሁሉም የኢትዮጵያ ልጆች ለሀገራቸው ልማትና ብልፅግና ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ ከመስራት ይልቅ ጥላቻና አምባገነንነት የአገዛዙ የአመራር ዘይቤ ሆኖአል” ብሎአል፡፡
“የሕዝብን ጥያቄ በሰላይ ጋጋታና በወታደር ብዛት ማዘግየት እንጂ መጨፍለቅ እንደማይቻል ከኢህአዴግ በላይ ምሳሌ ሊሆን የሚችል ድርጅት ሊኖር አይችልም፡” የሚለው አንድነት፣ በቅርቡ “አኬልዳማ” በሚል ርዕስ የቀረበው በጥላቻና በሽብር የተሞላ መርዘኛ የሆነ ፕሮፓጋንዳ በአንድ በኩል ጠቅላይ ሚኒሰትሩ በፓርላማ ተገኝተው በቂ ማሰረጃ ይዘን ነው ያሰርነው ላሉትና ይህንንም ተከትሎ በተለያየ ሁኔታ ለሚደርሰው ነቀፌታና ተፅዕኖ ድጋፍ ለመሰጠት፤ በሌላ መልኩ ደግሞ በኑሮ ውድነትና በመልካም አሰተዳደር ዕጦት የተማረረ ህዝብ በሰሜን አፈሪካና በመካከለኛው ምስራቅ ያለውን ህዝባዊ እንቅሰቃሴ ፈለግ ይከተላል በሚል ፍርሃት ቀድሞ ለማሰፈራራትና ወዮልህ ለማለት፤አልሞ የተነሣ ነው፡ “ሲል ገልጣል።
አንድነት አያይዞም የኢ.ቲ.ቪ. የሶስት ቀናት ፕሮፓጋንዳ እርስ በርስ የሚቃረን፣ በጥላቻ የታጨቀና ግልፅ የስም ማጥፋት ወንጀል የተፈፀመበት ፣ የአንድነት ፓርቲ አባላት ያልሆኑ ግለሰቦች እንደ ፓርቲው አባላት አድርጎ ያቀረበ ነው ሲል ኮንኖታል።
“አኬልዳማ” የተባለው የኢህአዴግ ፕሮፓጋንዳ በፍርድ ቤት የተያዘን ጉዳይ በቴሌቨዥን ፍርድ የተሰጠበት ተግባር ነው መሆኑን የሚያስታውሰው አንድነት ፣ አገዛዙ በህግ ሳይሆን በራሱ ሚዛን አሻባሪ ብሎ ዜጎችን የሚፈርጅ ከሆነ፣ የፍርድ ቤት አስፈላጊነት ምኑ ላይ ነው? የፍርድ ቤት ነፃነትስ ከየት ይመጣል? ሲል ይጠይቃል።
ኢ.ቲ.ቪ. ከእንዲህ ዓይነቱ በጥላቻ የታጨቀ አሰነዋሪና የወረደ ዘገባ ማስተላለፉ ከፍተኛ የሆነ የዕውቀት፣ የስነ ምግባር፣ የሞራል ውድቀት ላይ እንደሚገኝ ማሳያ ነው የሚለው አንድነት ፓርቲ፣ ህወሓት በረሃ በነበረበት ዘመን ባንክ ይዘርፍ እንደነበር በየአደባባዩ በኩራት የሚያወራው ጉዳይን ማንሳቱ አስቂኝ ነው ብሎአል።
የኢህአዴግ አሰኳል የሆነው ህወሓት ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን በኤርትራ ጉዳይ ላይ እያራመደው ያለው አቋም ሀገራችንን ትልቅ ዋጋ ማስከፈሉን፣ ሀገራችንን ወደብ አልባ እንድትሆን ያደረገው፣ ስልጣንን እንጂ የሀገርን ጥቅም ማዕከል አድርጎ ያለመሄድ በሽታ መሆኑን ያወሳው ፓርቲው፣ ኢህአዴግ ለሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት በቁርጠኝነት የሚታገለውን አንድነት ፓርቲን ከሻቢያና ከሸብርተኝነት ጋራ ለማገናኘት መሞከር ታላቅ ሰህተት ከመሆንም አልፎ ይህን ክስ ለመሰንዘር የሞራል ብቃት የለውም፡፡ ሲል አጣጥሎታል።
አገዛዙ የሕዝብን የለውጥ ፍላጎት በስለላና በጦር ኃይል እጨፈልቃለሁ የሚል አምባገነናዊ አካሄድ የቁልቁል ጉዞ እንደሚወስደው የሚጠቅሰው አንድነት ፓርቲ ፣ የኢህአዴግ አባላትም አመራሩ እየተንደረደረ እየሄደበት ካለው የመቀመቅ ጉዞ፣ ሀገርንም ፓርቲውንም አይጠቅምምና ተመለስ ሊሉት ይገባል ሲል ምክሩን ለግሷል።
በመጨረሻም ፓርቲው “የአገዛዙ ሟርተኛ ፕሮፓጋንዳ ሕዝብን የሚያሸብርና ወደ ደም መቃባት የሚወሰድ የእልህ ጉዞ መሆኑን ጠቅሶ፣ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀገራችን ካለችበት የፖለቲካ አዙሪት አንድትወጣ
ከፍርሃት ራሳችንን አውጥተን እጅ ለእጅ ተያይዘን ለዴሞክራሲና ለህግ የበላይነት የሚደረገውን ትግል እናግዝ ሲል ጥሪ አቅርቦአል።