በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ልማት ሕዝብን ተጠቃሚ የማድረጉ ጉዳይ በሕዝብ ጥያቄ እንደተነሳበት አንድ ጥናት አመለከተ

መጋቢት ፲፮ (አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እና በአዋጅ በፈረሰ ስያሜ የሚጠቀመው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድርጅት አዲስአበባን ጨምሮ በ20 ከተሞች አደረግነው ባሉት ጥናት በአገሪቱ እየተካሄደ ያለው ልማት አብዛኛውን ሕዝብ ተጠቃሚ የማድረጉ ጉዳይ ሙሉ በሙሉ እምነት አለኝ ያለው ሕዝብ እጅግ አነስተኛ መሆኑን አመለከቱ፡፡

አዲስ ዘመን ጋዜጣ በትላንትና ዕትም የፊት ገጽ ላይ “ዜጎች የኢኮኖሚ ዕድገቱ
በመንግስትና ሕዝብ ጥረት መገኘቱን እንደሚያምኑ አንድ ጥናት አረጋገጠ” በሚል ባቀረበው ዘገባ የጥናቱን ውጤት ይፋ አድርጓል፡፡ በዚሁ የጥናት ዘገባ መሠረት የኢኮኖሚ ዕድገት ስለመኖሩ ተጠይቀው ከፍተኛ ዕድገት አለ ያሉ 19.01 በመቶ ሲሆኑ መካከለኛ እድገት አለ ያሉ  58.17 በመቶ፣ ዝቅተኛ እድገት አለ ያሉ 13.37 በመቶ ሲሆኑ፣እድገት የለም ያሉ ደግሞ  5.44 በመቶ ናቸው ብሎአል፡፡

በአገሪቱ እየታየ ያለው የኢኮኖሚ እድገት አብዛኛውን ሕዝብ ተጠቃሚ አድርጓል ብለው ያምኑ እንደሆን ከተጠየቁት መካከል ሙሉ በሙሉ አምናለሁ ያሉት 19.68 በመቶ ሲሆኑ በከፊል አምናለሁ ያሉት  51.19 በመቶ፣ ሙሉ በሙሉ አላምንም ያሉት ደግሞ  15.95 በመቶ  ናቸው፡፡

አገሪቱ የያዘችው መሰረታዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ጉዞ አቅጣጫ ምን ይመስላል ተብለው ከተጠየቁት መካከል በጣም ጥሩ ነው ያሉት 33.14 በመቶ፣ ጥሩ ነው ያሉት 43.94 በመቶ፣ ጥሩም መጥፎም አይደለም ያሉት 13.09 በመቶ መሆናቸውን ጥናቱ ጠቁሞአል፡፡

የኢኮኖሚ ዕድገቱ ዋንኛ ምክንያትን በተመለከተ በቀረበው ጥያቄ 74.12 በመቶ የሚሆኑት የመንግስትና የሁሉም ዜጎች ያላሰለሰ ጥረት በማለት ምላሽ መስጠታቸውን ጋዜጣው በመጠቆም ይህንኑ ጉዳይ መሪ ዜና አድርጎ አቅርቦታል፡፡
በተጨማሪም ምክንያቱ የጥቂት ባለሃብቶች ጥረት ነው ያሉ 14.14፣በመቶ በዕድል የመጣ ነው ያሉ 2.58 በመቶ፣ መልስ ያልሰጡ 9.16 በመቶ መሆናቸውን አመልክቶአል፡፡

ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ባለሁለት አሃዝ ኢኮኖሚ እድገት አስመዝግቤአለሁ በማለት በተደጋጋሚ  ፕሮፖጋንዳ ቢያሰራጭም   በሕዝብ ኑሮ የሚገለጽ እድገት መታየት አለመቻሉን፣ ከዕድገት ይልቅ ሕዝቡ ለከፋ የኑሮ ውድነት መጋለጡን፣ በየደረጃው ተጠያቂነት ባለመስፈኑም መንግስት ለከፋ ሙስናና ብልሹ አሠራር መጋለጡን የዓለም አቀፍ ተቋማትን ጨምሮ የተለያዩ ወገኖች በየጊዜው የሚያነሱት ጉዳይ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡