(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 12/2011)በኢትዮጵያ የካቲት ወር ላይ የተመዘገበው አማካይ አገራዊ የዋጋ ግሽበት በ13 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
ኤጀንሲው ባወጣው መግለጫ ይፋ እንዳደረገው፣ ረዘም ያለ ጊዜ የዋጋ ግሽበት ሁኔታን በሚያሳይ የ12 ወራት ተንከባላይ አማካይ የዋጋ ግሽበትኝ በተመለከተ በተደረገው ምዘና፣ በዚህ ዓመት የካቲት ወር አገራዊ የምግብ የዋጋ ግሽበት በ11.7 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡
የ12 ወራት ተንከባላይ አማካይ አገራዊ ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች የዋጋ ግሽበትም በ14.4 በመቶ ጭማሪ አሳይተዋል ብሏል፡፡
በኢትዮጵያ የየካቲት ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት የካቲት ወር አኳያ ሲነፃፀር በ10.9 ከመቶ ከፍ ብሏል፡፡
የምግብ ዋጋ ግሽበት የየካቲት ወር 2011 ዓ.ም ካለፈው ዓመት የየካቲት ወር 2010 ዓ.ም ጋር ሲነፃፀር በ11.7 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡
ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀር ደግሞ ምግብ ነክ በሆኑ ምርቶች ረገድ በየካቲት ወር በቆሎና ጤፍ መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ እንዳሳዩ ተጠቁሟል፡፡ ስንዴ፣ ሩዝ፣ ገብስና ማሽላ ግን መጠነኛ ቅናሽ ማሳየታቸውንየማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ሪፖርት ያመላክታል፡፡
‹‹ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀር በፍራፍሬ፣ በሥጋ፣ በቅቤ፣ በወተት፣ በአይብና በዕንቁላል፣ እንዲሁም በቅመማ ቅመም ዋጋ ላይ ጭማሪ ተከስቷል፤›› ብሏል ኤጄንሲው።
እንደ ኤጄንሲው ገለጻ ምግብ ነክ ባልሆኑ የዋጋ መመዘኛ ክፍሎች በኩል የተያዘው ወር የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ11.2 በመቶ ጭማሪ ታይቶበታል፡፡
ምግብ ነክ ካልሆኑ የዋጋ መመዘኛ ጠቋሚ ክፍሎች መካከል የዚህ ወር የዋጋ ግሽበት ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከፍ እንዲል ካደረጉ ዋና ምክንያቶች በተለይ በናርኮቲክስና በአነቃቂ ዕፆች (በተለይም ጫት) ዋጋ ላይ የታየውን ጨምሮ ሌሎችም ምክንያቶች ቀርበዋል፡፡
በአልባሳትና መጫሚያዎች፣ በቤት ኪራይ፣ በቤት ክብካቤና በኢነርጅ (ማገዶና ከሰል) ቁሳቁሶች፣ በቤት ዕቃዎችና በቤት ማስጌጫዎች፣ በቤት መሥሪያ ዕቃዎች፣ በሕክምናና ትራንስፖርት (በተለይ በአውቶሞቢል) ዋጋ ላይ የታየው ጭማሪ ለግሽበቱ መንስዔ እንደሆኑ የኤጀንሲው ሪፖርት አመላክቷል፡፡
በሌላ በኩል በሁለት ወራት መካከል ባለው የአጭር ጊዜ የዋጋ እንቅስቃሴ መለኪያ ካለፈው ጥር ወር አኳያ የታየው ጭማሪ 0.3 በመቶ ብቻ ሆኗል፡፡ በኤጀንሲው ተጨማሪ ማብራሪያ መሠረት ወርኃዊ የዋጋ ግሽበት ምጣኔ የወቅቱን የዋጋ ሁኔታ የሚያሳይ በመሆኑ የአጭር ጊዜ ክስተት ብቻ አመላካች ተደርጎ እንደሚወሰድ ሪፖርተር ዘግቧል።