የካቲት ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የኢሳት የአዲስ አበባ ዘጋቢ እንዳለው ምርታቸውን ወደ ውጭ አገራት የሚልኩና የሚያስገቡ ነጋዴዎች ፣ መንግስት የጣለባቸውን የአባይ ግድብ ቦንድ ግዢም ሆነ ሌሎች የመንግስት እዳዎችን ለመክፈል የተቸገሩት ከውጭ ምንዛሬ እጥረት ጋር ተያይዞ ስራቸው በመዳከሙ ነው።
የተለያዩ የንግድ ድርጅቶች ኤልሲ ከፍተው እቃዎችን ለማስገባት በማይችሉበት ደረጃ ላይ በመድረሳቸው ድርጅታቸውን በመዝጋት ሰራተኞቻቸውን ለማሰናበት ጫፍ ላይ መድረሳቸውን ነጋዴዎች እንደሚገልጹ ዘጋቢያችን ገልጿል።
መንግስት የውጭ ምንዛሬ እጥረት የለም ቢልም ፣ ነጋዴዎቹ በበኩላቸው ካለፉት 7 ወራት ጀምሮ ኤልሲ ለመክፈት አለመቻላቸውን ይገልጻሉ።
የመንግስት የመገናኛ ብዙሀን ችግሩን የፈጠሩት ህገወጥ የገንዘብ ልውውጥ የሚያደርጉ ድርጅቶች ናቸው በማለት መንግስት እርምጃ እንዲወስድ ቢወተውቱም፣ መንግስት እስካሁን ድረስ እርምጃ አልወሰደም።
መንግስት ችግሩ በህገወጥ የገንዘብ አዘዋዋሪዎች የተፈጠረ ነው በማለት ከዚህ ቀደም የወሰደው እርምጃ ለውጥ አለማምጣቱ ፣ በድጋሜ ተመሳሳይ እርምጃ እንዳይወስድ አድርጎታል የሚሉ አስተያየቶች ይቀርባሉ።
በአገሪቱ የተከሰተው ከፍተኛ የዶላር እጥረት ወደ ውጭ የሚላከው የግብርና ምርት በከፍተኛ ደረጃ በማሽቆልቆሉ የተፈጠረ መሆኑን በቅርቡ በግብርና ሚኒስትሩ የቀረበው ሪፖርት እንደሚያሳይ ዘጋቢያችን ገልጿል።