ሚያዚያ ፳ (ሃያ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የተባበሩት መንግስታት አለም አቀፍ የጤና ድርጅትን ዋቤ ያደረገዉ መረጃ እንደሚገልፀዉ በኢትዮጵያ ከ100ሺህ እናቶች መካከል 676 የሚሆኑት በወሊድ ወቅት ህይወታቸዉን የሚያጡ ሲሆን በታዳጊ አገራት ካለዉ አማካይ ከ100 ሺህ እናቶች የ290 እናቶችን ሞት በእጥፍ የሚበልጥ ነዉ። በበለፀጉት አገራት ከ100ሺህ እናቶች በወሊድ ምክንያት ሕይወታቸዉን ሊያጡ የሚችሉት 14 ብቻ ናቸዉ።
በኢትዮጵያ 10 በመቶ የሚሆኑ እናቶች ብቻ የጤና አገልግሎት ባለበት በወሊድ የሚገላገሉ መሆናቸዉን በቅርቡ የተደረገ የህዝብ የጤና ጥናት ዉጤት የሚያመለክት ሲሆን ለዚህም ዋናዎቹ ምክንያቶች የእናቶች በሆስፒታል በሰለጠኑ የጤና ባለሙያዎች ስለሚሰጠዉ አገልግሎት ጠቃሚነት አለመረዳት፤ ባህላዊ እምነትና በገጠር አካባቢ የሚታየዉ የትራንስፖርት ችግር ለብዙ እናቶች ህይወት መጥፋት ምክንያት እንደሆኑ የመንግሰት ባለስልጣኖች እንደሚገልፁ አይሪን አመልክቷል።
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የወሊድ ጤና አገልግሎት ባለሙያ ፍሬወይኒ ገብረህይወት እንደጠቀሱት በኢትዮጵያ 80 በመቶ ለሚሆነዉ የእናቶች የወሊድ ወቅት ሞት የፊንጢጣ በሽታ፤ ኢንፌክሽን፤ ተገቢ እንክብካቤ የማይደረግበት የፅንስ ማስወረድ፤ የተዛባ የፅንስ አመጣጥ የሚያስከትለዉ የወሊድ ችግር፤ ኤች አይ ቪ ኤድስና ወባ እንደሆኑ ተናግረዋል።
የጤና ባለሙያ ርዳታ በማያገኙበት አወላለድ ከሚጠቀሙት ዉስጥ ቁጥራቸዉ 500ሺህ የሚሆኑ ሴቶችና ልጃገረዶች ህይወታቸዉን በሞት ባያጡም ፌስቱላን በመሰሉ ዉስብስብ የጤና ችግሮች ዉስጥ ሊወድቁ እንደሚችሉ የመንግስታቱ ድርጅት የመረጃ ምንጭ ያወጣዉ ዘገባ ይጠቁማል።
የተባበሩት መንግስታት የስነ ህዝብ ፈንድ በእርግዝና እና በወሊድ ወቅት ሊገጥሙ የሚችሉ ዉስብስብ የጤና ችግሮችን ለማስተናገድ ከአዲስ አበባ ወጣ ያሉ የጤና ተቋሞች በቂ የሰለጠነ የሰዉ ሃይል የሌላቸዉ፤ ወይንም አስፈላጊ መሳሪያና አቅርቦት እንደሚጎድላቸዉ አመልክቷል።
የመንግስታቱ ድርጅት የዜና አገልግሎት አይሪን ያቀረበዉ ይህ የኢትዮጵያ የጤና ጥበቃ መረጃ መንግስት በያጋጣሚዉ በጤና መስክ አስመዝግቤአለሁ ከሚለዉ ፕሮፖጋንዳ በእጅጉ ይቃረናል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide