ሐምሌ ፫ ( ሦስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአገር አቀፍ ደረጃ የሰብዓዊ መብት እና የዴሞክርሲ ግንባታ ላይ ለመስራት ፍቃድ ተሰጥቷቸው ሲንቀሳቀሱ ከነበሩ ከመቶ በላይ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ በአሁኑ ወቅት አምስቱ ብቻ ስራቸውን እየሰሩ መሆኑን ቪዥን ኢትዮጵያ ለዲሞክራሲ ጉባኤ ባዘጋጀው መድረክ ላይ ጥናቶች አመለከቱ።
ድርጅቶቹ እስከ ምርጫ 1997 ዓ.ም መባቻ ድረስ ስራቸውን በአግባቡ ያከናወኑ እንደነበርም ጥናቱ አመላክቷል። ከምርጫ 1997 ዓ.ም በኋላ በገዥው ህወሃት ኢህአዴግ ተረቆ ሥራ ላይ የዋለው የበጎ አድራጎት ሕግ ከወጣ በኋላ 95 ከመቶ በላይ የሚሆኑት ከስመዋል።
የድርጅቶችቹን እንቅስቃሴ የሚገድበው የበጎ አድራጎትና ማህበራዊ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ በአሁኑ ወቅት በጣት የሚቆጠሩ ብቻ ቀርተዋል። እነሱም በእጅጉ ደካማ ሆነዋል። ጨርሶም የመጥፋት አደጋ ከፊታቸው ተጋርጦባቸዋል ሲል ጥናታዊ ሪፖርቱ አመላክቷል። በጥናታዊ ውይይቱ ላይ ገዥው ፓርቲ እንደዚህ ዓይነት አፋኝ ሕጎችን ለማውጣት የተገደደው የምርጫ 1997 ዓ.ም አጋጣሚ መሆኑም የጥናታዊ ጽሁፉ ተወያዮች አስረድተዋል።
”ከ1997 ዓ.ም በኋላ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ላይ መስራት በመንግስት እንደ ፖለቲካ ስራ ተደርጎ መወሰዱ የችግሮቹ ሁሉ መነሻ ነው። የሲቪክ ማህበራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሚዲያ በሌለበት ስርአት ውስጥ ስለ ጠንካራ የዲሞክራሲ ስርአት ልንነጋገር አንችልም።” ሲሉ የሕግ ባለሙያው የሆኑት አቶ ደበበ ኃ/ገብርኤል ጥናታዊ ጽሁፋቸውን አቅርበዋል።
የሰብአዊ መብት ጥበቃ ስራ የፖለቲካ ስራ በመሆኑ ይሄ ሊሰራ የሚገባው በዜጎች እንጂ በውጭ እርዳታ ሊሰራ አይገባም በሚል አቋም የገንዘብ ምንጭ ላይ ገደብ የሚጥለው አዋጅ መውጣቱ የድርጅቶቹን ህልውና እንደተፈታተነውም ጥናታዊ ሪፖርቱ የሕጉን አፋኝነት በመረጃ አመላክቷል።
እየጠፉ ያሉት ድርጅቶች እንዲያገግሙ ከተፈለገ በ2001 ዓ.ም የወጣው የበጎ አድራጎትና ማህበራት አዋጅ መሻሻል እንዳለበት አጽንኖት በመስጠት ለገዥው ፓርቲ ተወካዮች መልእክታቸውና አስተላልፈዋል። የኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ ተወካይ በበኩላቸው ባለፉት 8 ዓመታት ውስጥ ብቻ 400 ያህል የበጎ አድራጎት ማህበራት ፈቃዳቸውን ሰርዘዋል።
በኢትዮጵያ በሰብዓዊ መብት እና በበጎ አድራጎት ስራዎች ላይ የተሰማሩትን ጨምሮ 3 ሺህ 185 ያህል ድርጅቶች እንዳሉ የተገለፀ ሲሆን ከምርጫ 1997 ዓ.ም በፊት ወደ 4700 የሚጠጉ እንደነበሩ ይታወሳል።