ኢሳት (መስከረም 9 ፥ 2009)
ነዋሪነታቸው በዚህ በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ከተማና የተለያዩ ግዛቶች የሆኑ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ መንግስት በመፈጸም ላይ ያሉ ግድያዎችንና አፈናዎችን በአስቸኳይ እንዲቆም በመጠየቅ ሰኞ በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ አካሄዱ።
ከመቼውን ጊዜ በላይ በቁጥር ልቀው የታዩት ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የአሜሪካ መንግስት ተደጋጋሚ ስጋትን ከመግለጽ ያለፈ ጠንከራ እርምጃ እንዲወስድ ሲያሳስቡ አርፍደዋል።
የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ በተካሄደበት ወቅት ዝናባማ የአየር ጸባይ ቢኖርም፣ በአካባቢው የተገኙ ኢትዮጵያውያን እየጣለ የነበረው ዝናብ ሳያግዳቸው የተለያዩ መልዕክቶችን ሲያስተላልፉ እንደረፈዱ ከስፍራው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
የዲሲ ግብረ ሃይል፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሃይማኖት ተቋማትና የሲቪክ ማህበራት በጋራ በመሆን ያካሄዱት ሰላማዊ ሰልፍ ከመቼውም ጊዜ በላይ ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ ህዝብ ማሳተፉንና የተሳካ እንደነበር አዘጋጆች ለኢሳት ገልጸዋል።
ከአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ወደተለያዩ አካባቢዎች የሚወስዱ ዋና ዋና ጎዳናዎች በሰልፉ ምክንያት ዝግ ሆነው የነበረ ሲሆን፣ ተጨማሪ የጸጥታ ሃይል እንዲሰማራ ተደርጎ እንደነበርም ለመረዳት ተችሏል።
ኢትዮጵያውያኑ ሲያሰሙ የነበረውን የተቃውሞ ጥያቄ ተከትሎ በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢትዮጵያን ጉዳይ የሚከታተሉ ተወካይ ከሰልፉ አዘጋጆች የቀረበን ጥያቄ በአካል በመገኘት ተቀብለዋል።
በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የተገደሉ ሰዎችን ምስል በማንገብ የተለያዩ መፈክሮችን ሲያስተጋቡ የነበሩ ሰልፈኞች ገዥው የኢህአዴግ መንግስት በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ እየፈጸመ ላለው ግድያና ተጠያቂነት እንደማያመልጥ ሲገልጹ ታይተዋል።
የአሜሪካ መንግስት በቅርቡ የኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች ከመጠን ያለፈ የሃይል ዕርምጃ በመውሰድ ላይ እንደሚገኝ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
በሁለቱ ክልሎች ይፈጸማል ያሉትን የጅምላ ግድያና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለማውገዝ በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፊት ለፊት ተሰባስበው የነበሩት ኢትዮጵያውያን የአሜሪካ መንግስት አምባገነን መንግስት ከመደገፍ ተቆጥቦ ለዴሞክራሲ መስፈን ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር እንዲያሳይ ጠይቀዋል።
“የኦሮሞ ደም የአማራ ደም ነው የአማራ ደም የኦሮሞ ደም ነው” የሚሉ ድምጾች ሲያሰሙ የነበሩት ኢትዮጵያውያን የህዝቦች አንድነት በገዥው የኢህአዴግ መንግስት ሴራ አይከፋፈልም ሲሉ ያላቸውን ተቃውሞ አሰምተዋል።
በ25 ማህበራት አስተባባሪነት የተዘጋጀው ይኸው የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ፣ ከ1997ቱ ምርጫ በኋላ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን አሳትፎ ሲካሄድ ከጥቂቶቹ አንዱ እንደሆነም አዘጋጆቹ አስረድተዋል።
በሰልፉ ምክንያት በኪሎሜትሮች የሚቆጠር ዋና ዋና ጎዳና ዝግ ሆነው ለሰዓታት ያህል ያረፈደ ሲሆን፣ የሰልፉ አዘጋጆች ከፓርላማ አባላት ጋር ውይይትን ለማካሄድ ቀጠሮ ተይዞላቸው እንደነበር ታውቋል።
ነዋሪነታቸው በዚህ በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ከተማ ከሆነ ኢትዮጵያውያን በተጨማሪ በርካታ ሰዎች የተለያዩ የትራንስፖርት አገልግልቶችን በመጠቀም ከተለያዩ ግዛቶች ተሳታፊ እንደነበሩም ታውቋል።
በተመሳሳይ ሁኔታም ሰኞ ነዋሪነታቸው በእስራዔል ቴላቪቭ ከተማ የሆነ ኢትዮጵያውያን በከተማዋ በሚገኝ የአሜሪካ ኤምባሲ በመገኘት የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ማካሄዳቸውን ከስፍራው ለኢሳት የደረሰ መረጃ አመልክቷል።
በኢትዮጵያ መንግስት የሚፈጸሙ ግድያዎች እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በአስቸካይ እንዲቆም የተጠየቁት ኢትዮጵያውያኑ የአሜሪካና የእስራዔል መንግስታት በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጫናንን እንዲያደርጉ አሳስበዋል።