ነሃሴ ፲፰ ( አሥራ ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ካለፈው መጋቢት ወር ጀምሮ ከመጠን በላይ በሚጥለው ዝናብ በተፈጠረ የጎርፍ መጥለቅለቅ ሳቢያ ከ600 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን ከትውልድ ቀያቸው ተፈናቅለዋል። የጎርፍ አደጋው እስከ ቀጣይ ዓመት ታህሳስ ወር ድረስ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል።በኢትዮጵያ ዝናቡ ወቅቱን ጠብቆ አለመጣሉን ተከትሎ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ባለፉት አስር ዓመታት ውስጥ ተከስቶ የማያውቅ አስከፊ የርሃብ አደጋ አንዣቧል። በድርቁ ሳቢያ ከ10ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለርሃብ በመጋለጣቸው አፋጣኝ የሆነ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ተመድ አክሎ ገልጿል።
ከባለፈው መጋቢት ወር ጀምሮ እስከ ሰኔ ወር ብቻ ቁጥራቸው ከ300 ሺህ በላይ ዜጎች በጎርፍ ምክንያት ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ቀውስ ጥናት አረጋግጧል።በተጨማሪም ቀሪዎቹ ደግሞ በኦሮሚያና በሶማሊያ ክልል የድንበር ግጭቶች ምክንያት ከትውልድ ቀያቸው መፈናቀላቸውን ድርጅቱ አመላክቷል። ከመኖሪያቸው ከተፈናቀሉት ኢትዮጵያዊያን ውስጥ 10 ሺህ በላይ ቤተሰቦች የሚሆኑ አሁንም ወደ ቀያቸው ያልተመለሱ ሲሆን አፋጣኝ የምግብና የመጠለያ እርዳታ ያሰፈልጋቸዋል። በሶማሊያ ክልል ነዋሪ የሆኑ በድርቁ ተጠቂ ከ85 ሺህ በላይ ዜጎችን ለማገዝ እንዳይቻል የጎርፍ አደጋው አሁንም እክል እየፈጠረ ነው።
ላሊና የተባለው አዲሱ የዓየር ለውጥ መዛባት በተለይ በኢትዮጵያ ተጨማሪ የጎርና የዝናብ አደጋዎችን እንደሚያደርስ ተመድ አስታውቋል። ላሊና በኢኳቶሪያል ፓስፊክ ውቂያኖስ ባልተጠበቀ ሁኔታ በሚፈጠር ቅዝቃዜ ምክንያት በሰባት ዓመታት ውስጥ ለሁለት ጊዜያት የሚከሰት የዓየር መዛባት ነው። ላሊና ከነሃሴ ወር ጀምሮ የተፈጠረ ክስተት ሲሆን በኤሊኖ የአየር መዛባት ወቅት በከፍተኛ አካባቢዎች ከመጠን በላይ የሆነ ዝናብ እንዲዘንብ በማድረግ ከፍተኛ ጎርፍን ያስከትላል። የላኒና ዓየር መዛባት በኢትዮጵያ በተለይ በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች ከፍተኛ አደጋ እንደሚያደርስ የተባበሩት መንግስታትን በመጥቀስ ሮይተርስ ዘግቧል።