የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅት አባላትንና ዜጎችን ማሰሩ ቀጥሎአል

ነሃሴ  ፲፰ ( አሥራ  ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በምእራብ ጉጂ ዞን ገላና ወረዳ የሰማያዊ ፓርቲ አስተባባሪ የሆኑት አቶ አራርሶ ጌዶ ትናንት ማክሰኞ በርቲ ቀበሌ ውስጥ ተይዘው ታስረዋል።

በአዲስ አበባ 4ኛ ፖሊስ ጣቢያ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ 56 ወጣቶች ታስረው ከፍተኛ ደብደባ የደረሰባቸው ሲሆን ፣ ምግብ ከቀመሱ በርካታ ቀናትን ያስቆጠሩ በመሆኑ ህይወታቸው አደጋ ላይ ወድቋል።

ብዙዎቹ በጠጠር እና እሾህ ላይ በባዶ እግራቸው እንዲሄዱ፣ ውሃ ውስጥ እንዲገቡ ከተደረጉ በሁዋላ እንደሚገረፉ እንዲሁም በረሃብ እንዲቀጡ በመደረጋቸው ብዙዎች መልካቸው ሙሉ በሙሉ ተለውጦ በሞትና በህወሃት መካከል እንደሚገኙ ምንጮች ገልጸዋል።

ፖሊሶች እስረኞችን ለማስፈታት እስከ 15 ሺ ብር ጉቦ መቀበል መጀመራቸውንም ዘመዶቻቸውን ያስፈቱ ሰዎች ለኢሳት ገልጸዋል። በአዋሽ አርባ፣ ብር ሸለቆ እና ሌሎችም ወታደራዊ ካምፖች ውስጥ የታሰሩ ወጣቶች ፣ የስርዓቱ ተቆርቋሪ በሆኑ ነባር ታጋዮች ብቻ ቁም ስቅላቸውን እያዩ በመሆኑ አለማቀፍ ቀይ መስቀል ጉዳያቸውን እንዲያይላቸው ኢሳት ግፊት እንዲያደርግላቸው ተማጽነዋል።