ኢሳት (ጥር 22 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ ተከስቶ ባለው አዲስ የድርቅ አደጋ መጠነ ሰፊና የከፋ የምግብ እጥረት በመከሰት ላይ መሆኑን በስፍራው የሶስት ቀናቶችን ጉብኝት ያደረጉት የተባባበሩት መንግስታት ድርጅት የአስቸኳይ የእርዳታ ማስተባበሪያ ሃላፊዎች ገለጹ።
በሶማሊ ክልል ስር በሚገኙ የተለያዩ ዞኖች የድርቁ ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን የገለጹት የተቋሙ ሃላፊ ስቴፍን ኦ’ብሪያን በተመለከቱት ነገር እጅግ ማዘናቸውንና ድርቁ የከፋ የምግብ እጥረት ማስከተሉን ይፋ አድርገዋል።
የአለም አቀፍ ማህብረሰብ ድርቁ እያደረሰ ላለው ጉዳት ጊዜን ሳይወስዱ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጡም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአስቸኳይ ጊዜ የእርዳታ አስተባባሪው ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
የሚባክን ጊዜ መኖር የለበትም ሲሉ ያሳሰቡት ሃላፊው በርካታ የቤት እንስሳት በመሞት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። ጉብኝታቸውን ተከትሎ ለአለም አቀፍ ማህብረሰብ ጥሪያቸውን ያቀረቡት ኦ’ብሪያን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወት አደጋ ውስጥ መሆኑን አስታውቀዋል።
ካለፈው አመት ሃምሌ ወር ጀምሮ በሶማሌ፣ ኦሮሚያ፣ አፋርና የደቡብ ክልሎች ስር በሚገኙ በርካታ ወረዳዎች የተከሰተው አዲስ የድርቅ አደጋው ወደ ስድስት ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ለአስቸኳይ የምግብ ድጋፍ እንዲጋለጡ ማድረጉ ይታወሳል።
ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ያለውን ይህንኑ አዲስ የድርቅ አደጋ ለመታደግ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የኢትዮጵያ መንግስት የ948 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ጥሪን አቅርበዋል።
ድርቁን ለመታደግ እየተደረገ ያለው ጥረት አፋጣኝ ርብርብ ካላገኘ የተረጂዎች ቁጥር እየጨመረ ሊሄድ እንደሚችልና ድርቁም በሰዎች ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት የከፋ ይሆናል ተብሎ ተሰግቷል።
በዚሁ የድርቅ አደጋ ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ህጻናትን ቁጥር እየጨመረ መሆኑን የተናገሩት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአስቸኳይ ጊዜ የእርዳታ ማስተባበሪያ ሃላፊ ስቴፋን ኦ’ብሪያን የምግብ እጥረቱ ወደ አሳሳቢ ደረጃ ሊሸጋጋር እንደሚችልም ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ ላይ አሳስበዋል።
አዲሱ የድርቅ አደጋ ጉዳት እያደረሰባቸው ባሉ አካባቢዎች እስካሁን ድረስ ወደ 600 የሚጠጉ ትምህርት ቤቶች የተዘጉ ሲሆን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ህጻናት ተማሪዎችም ከትምህርት ውጭ መሆናቸው ተመልክቷል።
የመንግስት ባለስልጣናት በበኩላቸው በአራቱ ክልሎች ጉዳት እያደረሰ ያለውን የድርቅ አደጋ ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ቢገልጹም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሃላፊዎች በስፍራው የከፋ የምግብ እጥረት በመባባስ ላይ መሆኑን ይፋ አድርገዋል።
ባለፈው አመት በስድስት ክልሎች ተከስት በነበረው የድርቅ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸው ዞኖች በአዲሱ የድርቅ አደጋ ዳግም በመመታታቸው ሳቢያ ጉዳዩ አሳሳቢ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አክሎ አስታውቋል።
ከ10 ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን በስድስት ክልሎች ተከትሎ በነበረው የድርቅ አደጋ ለአስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ተጋልጠው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት 5.6 ሚሊዮን ሰዎች ለተመሳሳይ ችግር መጋለጣቸው ለመረዳት ተችሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የአለም አቀፍ የህጻናት አድን ጥምረት ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በጎረቤት ሶማሊያና ኬንያ 6.5 ሚሊዮን የሚሆኑ ህጻናት ለከፋ የምግብ እጥረት ሊጋለጡ እንደሚችሉ ሰኞ ማሳሰቡን አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃና ዘግበዋል።
በቀጠናው ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ እየተባባሰ ሊሄድና በሶስቱ ሃገራት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህጻናት ለከፍተኛ የረሃብ ብሎም የሞት አደጋ ሊደርስባቸው እንደሚችል በኢትዮጵያ የብሪታኒያ የህጻናት አድን ድርጅት ሃላፊ የሆኑት ጆን ግራም ይፋ ማድረጋቸው የኬንያው ካፒታል ኒውስ ጋዜጣ ዘግቧል።
በኢትዮጵያ ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ተጋልጠው ከሚገኙ ስድስት ሚሊዮን ሰዎች ጎን ለጎን በሶማሊያና ኬንያ አጠቃላይ 15 ሚሊዮን ሰዎች ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ተጋልጠው እንደሚገኙም የህጻናት አድን ጥምረት አስታውቋል።
የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ከዚህ በፊት በሃገሪቱ የደረሰው የከፋ የድርቅ አደጋ በድጋሚ ጉዳት እንዳያደርስ አፋጣኝ ርብርብ ማድረግ እንዳለበትም የህጻናት አድን ድርጅቶቹ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።