በኢትዮጵያ ለውጭ አገር ባለሀብቶች የሚሰጡት ሰፋፊ የእርሻ መሬቶች ዋጋ ተገቢ ነው ሲሉ ወ/ሮ ገነት ዘውዴ ተናገሩ

ጥቅምት ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ኦል አፍሪካ ዶት ኮም እንደዘገበው በህንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ወ/ሮ ገነት በኢትዮጵያ የጠረፍ አካባቢዎች በቂ የሆኑ የመሰረተ ልማቶች ያልተዘረጉ በመሆኑና ሰው ሀይልም በበቂ ሁኔታ አለመገኘቱ፣ እንዲሁም አንዳንድ አገሮች ባለሀብቶችን ለመሳብ መሬት በነጻ የሚሰጡ በመሆኑ በኢትዮጵያ የእርሻ መሬቶችን ለውጭ ባለሀብቶች በርካሽ ዋጋ መሸጡ ተገቢ ነው ሰሉ የመንግስታቸውን አቋም አጠናክረዋል።

ወ/ሮ ገነት ይህን ይበሉ እንጅ መንግስታቸው በውጭ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ከአለማቀፍ ድርጅቶች በሚሰነዘርበት ተቃውሞ የተነሳ፣ የእርሻ መሬዎችን ዋጋ በመከለስ ላይ ነው።

በአለም በየትኛውም አካባቢ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያ የእርሻ መሬት የሚከፍሉት ዋጋ በሄክታር በአመት 10 ብር ነው። ከሁሉም በላይ የከፋው ነገር ባለሀብቶቹ ከኢትዮጵያ ያመረቱትን ምርት ለአገር ውስጥ ገበያ ከማቅርብ ወደ ውጭ አገራት መላካቸው ነው በማለት አለማቀፍ የሰብአዊ መብቶት ተቋማት ሰይቀሩ ክሶችን ያሰማሉ።

ወ/ሮ ገነት የውጭ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የተጠፈጥሮ ሀብት ላይ ውድመት እንደማያደርሱም ገልጸዋል። ይሁን እንጀ አለማቀፍ ተቋማት ባለሀብቶቹ ለተፈጥሮ ሀብቶች ግድ የላቸውም በማለት ክስ ያሰማሉ።

አንድ የህንድ ባለሀብት በኢትዮጵያ የሚከፈለውን የመሬት ኪራይ ለመግለጽ ” መሬቱን ውሰዱ አሉን” ወሰድን በማለት መግለጹ ይታወሳል