በአማራ ክልል ነጋዴዎች በዘፈቀደ በሚጣለው ግብር እየተማረሩ ነው

ጥቅምት ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ለኢሳት የሚደርሱ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ነጋዴዎቹ በበቂ ጥናት ባልተደገፈ መልኩ በሚጣልባቸው ግብር በመማረር የንግድ ድርጅቶቻቸውን እየዘጉ፣ ወደ አዲስ አበባ ወይም ወደ ጎረቤት አገሮች በተለይም ወደ ደቡብ ሱዳን በመጓዝ ላይ ናቸው ።

መንግስት የአምስት አመቱን የልማት ግቦች አሳካለሁ በማለት የጀመረው እቅድ በገንዘብ እጥረት ምክንያት ፈተና ውስጥ እየወደቀ መምጣቱን በመመልከቱ ፣በነጋዴው ላይ ግብር ለመቆለል መገደዱን ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በ አማራ ክልል የሚኖረው ሁሴን ቢላል የተባለው ወጣት ነጋዴ ለኢሳት እንደገለጠው እርሱ በሚኖርበት አካባቢ ነጋዴዎች ከገቢያቸው ከ10 እስከ 20 እጥፍ እንዲከፍል ተገዷል::

አይ ኤም ኤፍ በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት የኢትዮጵያ መንግስት ሰፋፊ ፕሮጀክቶችን ለመስራት የነደፈው እቅድ በነጋዴው ላይ ጫና ፈጥሮ ኢኮኖሚውን እንዳይጎዳው አስጠንቅቆ ነበር።

በሌላ ዜና ደግሞ በአዲሱ የበጀት ዓመት በመጀመሪያዎቹ ወራት ከውጪ ንግድ ገቢ ይገኛል ተብሎ የታቀደው ገቢ በ 40 በመቶ አካባቢ ቅናሽ ማሳየቱን ከንግድ ሚኒስቴር የወጣ መረጃ አመለከተ።

እንደ ሚኒስቴሩ  መረጃ፤በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከውጪ ንግድ ገቢ የተገኘው ገንዘብ 475 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፤ይህም  በተጠቀሰው ጊዜ ይገኛል ተብሎ  በዕቅድ ከተያዘው  61 በመቶውን ብቻ የሚሸፍን ነው።

መንግስት በ 2005  የበጀት ዓመት በጠቅላላ ከውጪ ንግድ 5 ቢሊዮን ዶላር ለመሰብሰብ ማቀዱን የጠቆመው መረጃው፤ይሁንና በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ወራት ዕቅድና አፈፃፀም መካከል ይህን ያህል የሰፋ ልዩነት መታየቱ ፤የተያዘው አጠቃላይ እቅድ ከወረቀት ነብርነት የማይሻገር እንደሆነ ያመለክታል።

የሚኒስቴሩ መረጃ በቀጣይም ወራቶች በ ዕቅድና በአፈፃፀሙ መካከል የዚህን ያህል ክፍተት ከታዬ አጠቃላይ በበጀት ዓመቱ ይገኛል ተብሎ የታሰበው ገቢ ላይሰበሰብ ይችላል የሚል ስጋት አሳድሯል ይላል።

የሚኒስቴር መስሪያ ቤት ሀላፊዎቹ ከዘርፉ ሠራተኞች ጋር በቅርቡ ባደረጉት ስብሰባ የበጀት ዓመቱን እቅድ ለማሳካት ሁሉም ባለ በሌለ ሀይላቸው እንዲረባረቡ ማሣሰቢያ መስጠታቸው ይታወሳል።

ሠራተኞቹ  ግን፦  እቅዱ እጅግ የተጋነነ መሆኑን በመጥቀስ፤በልክ ሳይታቀድ መመሪያ በማውረድ ብቻ  የተፈለገውን ያህል ገቢ መሰብሰብ እንደማይቻል ተናግረዋል።

ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር  አቶ መለስ ዜናዊ የአምስት ዓመት  የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ  ብለው ከአገሪቱ አቅም በላይ የሆኑ እቅዶችን እንደ ድንገት  ባወጁበት ጊዜ  አንዳንድ ወገኖች <በእርግጥ እቅዱን ታሳኩታላችሁ ወይ?> በማለት በእቅዱ ስኬታማነት ላይ ያላቸውን ጥርጣሬ እንደሚገልጹላቸው ከጠቀሱ በሁዋላ፦< ከፍ አድርገን እናቅዳለን፤ ዕቅዱን ሙሉ በሙሉ ባናሳካም ፤የቻልነውን ያህል ለመስራት እንሞክራለን”ማለታቸው  ይታወሳል።

ከዚያ ወዲህ የማይሳኩ እቅዶችን ለጥጦ ማቀድና  ዕቅዱ ባይሳካም እስከሚቻለው ድረስ መሞከር የሚል አዲስ ነገር በየዘርፉ እየተለመደ መምጣቱን  የመንግስት ሠራተኞች ሲናገሩ ይደመጣሉ።

ይህ ነገር  መለመዱም፤  የእቅድ አሠራርን በማጥፋትና ተጠያቂነት እንዳይኖር በማድረግ ለሥራው ሀላፊዎች የሙስና በር ከመክፈቱም በላይ ጥሩ የስንፍና ምክንያት እየሆናቸው ነው ብለዋል-ሠራተኞቹ።

አክለውም፦<<እንኳን አገርን ያህል ነገር የግል ህይወትም ያለ እቅድ አይመራም።ለዕድገት ወሳኙ በአግባብና በልክ እያቀዱ- በእቅዱ መሰረትና ከዚያ በላይ የሠሩትን እያበረታቱ፤ከዚያ በታች የሠሩትን  ደግሞ እየጠየቁ የመሥራት ባህልን ማዳበር ነው፤ በዘፈቀደ እያቀድን እስከምንችለው እንሂድ ማለት፤ ውጤቱ ውድቀት ነው>>ሲሉም አዲስ በተያዘው ፈሊጥ ላይ ያላቸውንም ስጋት ገልፀዋል።

የ 5 ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ከተነደፈ ሁለተኛ ዓመቱ እየተገባደደ ቢሆንም፤ በዕቅዱ የተካተቱት እንደ ህዳሴው ግድብና የባቡር ሀዲድ ግንባታ የመሳሰሉ ታላላቅ እቅዶች ገና ከመነሻቸው አልተንቀሳቀሱም።