ታህሳስ ፪(ሁለት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአዲስ አበባ አንዳንድ አካባቢዎች እና በሰሜን የአገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ ከተሞች መብራት በተደጋጋሚ እየተቋረጠ ሲሆን፣ መብራት ሀይል የተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ተናበው ለመስራት አልቻሉም በሚል ወቀሳ አሰምቷል። በጉዳዩ ዙሪያ ዘጋቢያችን ያነጋገራቸው የኢትዩጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ 40 በመቶ የሚሆነው ኤሌክትሪክ ሃይል መቆራረጥ የሚፈጠረው በሰው ሰራሺ አደጋ ነው ያሉ ሲሆን፣ ከአዲስ አበባ መንገድ እና ትራንስፖርት ባለሰልጣን ጋር ተናበን መስራት ባለመቻላችን በዚህ አራት ወራት ብቻ የኤሌክትሪክ ባቡር መስመር ዝርጋታ በሚል ሰበብ ከ120 ሚልዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ወድሞብናል ብለዋል፡፡
በቅርቡ በቦሌ ሩዋንዳ በኮንክሪት የተገነባው ባለ 33 ኪሎ ቮልት ትራንስፎርመር እና መሰል እቃዎች የ በአዲስ አበባ የመንገድ ስራ ድርጅት የመንገድ ቁፋሮ ሃለፊነት በጎደለው ሁኔታ ከስሩ በመጣላቸው ከ450 ሺ ብር በላይ ንብረት መውደሙን ገልጽዋል፡፡
የአዲስ አበባ መንገድ እና ትራንስፖርት ባለስልጣን በሚፈጥረው ችግር ደንበኞችን ማርካት አልቻልም በዚህም የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ ደንበኞች ሮሮ እያሰሙ ነው በማለት ሀላፊው ተናግረዋል።
በተያያዘ ዜናም ከባህር ዳር አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት በምትገኝ ይነሴ የገጠር ቀበሌ በ66 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ተሸካሚ ሰባት የብረት ታዎሮች በመዘረፋቸው በዚህ የኤሌክትሪክ መሰመር ሃይል የሚያገኙ በዳንግላ እና ፓዊ ሳብስቴሺን የሚገኙ ደንበኞች ሃይል አጥተዋል ፡፡ ምእራብ ጎጃም በከፊል መራዊ ፤ ቢኮሎ ፤ ዱርቤቴ ፤ይስማላ ፤ሊበን ፤ቁንዝላ ፤ዲንካራ ፤ በሰሜን ጎንደር ሻውራ እና አካባቢው ፤ በአዊ ዞን ዳንግላ ፤ቲሊሊ ፤ እንጅባራ አዲስ ቅዳም ፤ግምጃ ቤት ፤መተክል ፤ ሰከላ፤ በቢንሻንጉል ጉምዝ መተከል ዞን በሙሉ በጨለማ ውስጥ መሆናቸውን አቶ ምስክር ነጋሺ ተናግረዋል፡፡
ኮርፖሬሺኑ ችግሩን ለመፍታት እየሰራሁ ነው ቢልም እስካሁን ድረስ የታየ ለውጥ የለም