ጥር ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በአዲስ አበባ ዩነቨርሲቲ የሥነ ምድር ትምህርት ክፍል የከርሰ ምድር ውኃን በተለያዩ መንገዶች ሲያጠኑ የቆዩ አንድ ምሁር ባወጡት ጽሁፍ አብዛኛው የአዲስ አበባ ወንዞች ለመጠጥም፣ ለእርሻም፣ ለኢንዱስትሪም መዋል የሚችል አይደለም።
በአገር አቀፍ ደረጃ የሚገኙ አዋሽ፣ ቦረከናና ሌሎች ወንዞች ከኢንዱስትሪዎችና ከከተሞች በሚወጡ ቆሻሻዎች መበከላቸው ተመልክቷል፡፡
ከሽንት ቤት ጉድጓዶች የሚወጡ ፍሳሾች፣ ከኢንዱስትሪዎች የሚወጡ ኬሚካሎችና የሳሙና እጣቢዎች ወደ ከርሠ ምድር በመዝለቅ ውኃውን የሚበክሉት በመሆኑ፣ በከተሞች አቅራቢያ የሚገኙ የከርሠ ምድር ውኃዎች በሙሉ በባክቴሪያ እና በኬሚካል እንዲበከሉ አድርጓቸዋል።፡፡በተለይ ሽንት ቤቶች የፍሳሽ ማስወገጃ መስመር ስለሌላቸው በቀጥታ ወደ ከርሠ ምድር ውኃ ጋር በመቀላቀል የሚያደርሱት ብከላ የጎላ ነው፡፡ እንደ መሀል አዲስ አበባ፣ አቃቂ፣ ደብረ ዘይት፣ ሞጆ፣ ናዝሬትና ሌሎች ከተሞች ላይ የዚህ ዓይነቱ ብክለት በአስጊ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
ባጠኗቸው ጥናቶች መሠረት በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ የውኃ ብክለት ደረጃ ከሕዝቡ ብዛት፣ ከፋብሪካዎች ቁጥር መበራከትና ከእርሻዎች መስፋፋት ጋር ተያይዟል፡፡ ከርሠ ምድር ውኃን በተመለከተ ኅብረተሰቡ ሃብቱን እንደ ራሱ ንብረት ካለመቁጠር ጋር ተያይዞ ለብክለት በመጋለጥ ላይ ነው፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ መስመር በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ የተሠራ ነው፡፡ መስመሩ ከስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ተነስቶ በአራት ኪሎ በኩል ቤተመንግሥት አድርጎ ቦሌ ሲደርስ፣ ሁለተኛው መስመር ደግሞ ከአሮጌው አውሮፕላን ማረፊያ በመነሳት በልደታ በኩል በማለፍ ከመጀመሪያው መስመር ጋር በመያያዝ ቃሊቲ ወደሚገኘው ማጣሪያ ይገባል፡፡
የአቃቂ ከርሠ ምድር ውኃ የሚገኝበት ሥፍራ በኢንዱስትሪ ዞንነት መከለሉ ተጨማሪ ስጋትን ፈጥራል ። ከዚህ የከርሠ ምድር የሚገኘው ውኃ እጅግ ዘመናዊ በሆነና በኮምፒውተር ቴክኖሎጂ በተደገፈ መንገድ ተጣርቶ ነው ለሕዝቡ ቢቀርብም፣ አሁን በአካባቢው እየተቋቋሙ ያሉት ፋብሪካዎች በውኃው ላይ አደጋን ደቅነዋል፡፡ ከእነዚህ ፋብሪካዎች የሚለቀቁ ኬሚካሎች ወደ ከርሠ ምድር ውኃው እየገቡ ነው፡፡
መንግስትና ህዝቡ ለከርሰ ምድር ውሀ ብከለት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እርምጃ ካልወሰዱ ከፍተኛ ጉዳት ሊደርስ እንደሚችል ምሁራኑ ያስጠነቅቃሉ:፡