(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 10/2010) በሃገሪቱ መንግስታዊ መዋቅር ውስጥ በመግባት ስራዎችን እንዲመሩ እና እንዲያስተባብሩ በኢሕአዴግ የተዋቀሩት 12 ግብረ ሃይሎች እንዲፈርሱ መወሰኑ ተገለጸ።
እነዚህ ግብረሃይሎች በአቶ በረከት ስምኦን፣አቶ አባዱላ ገመዳ እና በሕወሃት ሰዎች የሚመሩ እንደነበሩም ታውቋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረውን ቀውስ ተከትሎ የኢሐዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በታህሳስ ወር 2010 በወሰነው መሰረት ተዋቀረ የተባለው ኮሚቴ የካቢኔ ድልድልን ጨምሮ ፣በመንግስት ስራ ውስጥ በግልጽ ጣልቃ የሚገባ እና ሒደቶችን በበላይነት የሚያስተባብር እንደነበርም ተመልክቷል።
በመንግስት እና በገዢው ፓርቲ መገናኛ ብዙሃን በቀረበው ዘገባ መሰረት እንዚህ ግብረሃይሎች ፈርሰው የሚመለከታቸው አካላት ስራዎቹን እንዲከውኑ ተወስኗል።
ግብረ ሃይሎቹ እንዲፈርሱ የተወሰነው መንግሥት የግብረ ሃይሎቹን አፈጻጸም ከገመገመ በኋላ የህዝቡን ጥያቄዎች በአጥጋቢ ሁኔታ ለመፍታትና ሀገሪቱ ያጋጠሟትን ችግሮች ውጤታማ በሆነ መንገድ መፍታት የሚቻለው በተደራጀ ተቋማዊ አፈጻጸም መሆኑን በመገንዘቡ ነው ተብሏል።
በመሆኑም ግብረ ሀይሎቹ እስካሁን ሲያከናውኗቸው የነበሩትን ሥራዎች በቀጥታ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ተቋማት እንዲያስረክቡ በመንግሥት መወሰኑን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።
ይህ 12 ግብረ ሃይል የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን አስተዳደር አያሰራም በሚል በፖለቲካ ተመልካቾች ሲተች ቆይቷል፣ይህ ግብረ ሃይል መዋቀሩን እና በእነማን እንደሚመራ ኢሳት ተከታታይ ዘገባ ማቅረቡም ይታወሳል።