(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 16/2010) በኢሉባቡር መቱ ከተማ ከአንድ የህወሀት አባል መኖሪያ ቤት በርካታ የጦር መሳሪያዎችና የቅስቀሳ በራሪ ወረቀቶች ተገኙ።
በከተማዋ ለረጅም ጊዜ ነዋሪ በሆኑትና በህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ አባልነታቸው የሚታወቁት ግለሰብ በመኖሪያ ቤታቸው በተደረገ ፍተሻ ዘጠኝ ቦምቦችን ጨምሮ ክላሽ መሳሪያዎች፣ የጦር ሜዳ መነጽር፣ ለቅስቀሳ የተዘጋጁ በራሪ ወረቀቶችና የተለያዩ ዶክመንቶች እንደተገኙ ለማወቅ ተችሏል።
በሌላ በኩል በኢሉባቡር በደሌና ጮራ በህወሀት መንግስት አቀናባሪነት የተፈጸመው ጥቃት በመቆሙ አካባቢው መረጋጋቱን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
አቶ ሃይለኪሮስ ገብሩ አሸብር ይባላል። በኢሉባቡር መቱ ከተማ ነዋሪ ናቸው።
በንግድ ስራ የሚተዳደሩት አቶ ሃይለኪሮስ የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ህወሀት አባልም ናቸው።
ሰሞኑን በኢሉባቡር በደሌና ጮራ ወረዳዎች የተከሰቱትን ጥቃቶች ተከትሎ በተነሳው ጥርጣሬ መኖሪያ ቤታቸው እንዲፈተሽ በኦሮሚያ ክልልና በመቱ ከተማ ፖሊስ ወሳኔ ላይ ይደረሳል።
የመቱ ከተማ ነዋሪዎች ባሉበት ፖሊስ ባደረገው ፍተሻ ከመኖሪያ ቤታቸው በርካታ የጦር መሳሪያዎችና ዶክመንቶች ተገኙ።
ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ህወሀት የሚመራው የደህንነት መስሪያ ቤት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ለሚፈጠሩ ግጭቶች በቀጥታ እጁ እንዳለበት መረጃዎች እየወጡ ባለበት በዚህን ወቅት በአቶ ሃይለኪሮስ መኖሪያ ቤት የተገኙት መሳሪያዎች ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኗል።
የኢሳት የመረጃ ምንጮች እንደገለጹት በአቶ ሃይለኪሮስ መኖሪያ ቤት በሌላ ዝግ በሆነ ክፍል ውስጥም መሳሪያዎች ሳይደበቁ አይቀርም በሚል ፖሊስ ለመክፈት እንደተዘጋጀ ተገልጿል።
በሌላ በኩል ባለፈው ቅዳሜ በበደሌና ጮራ ወረዳዎች በህወሀት አቀናባሪነት ተፈጽሞ የነበረው ጥቃት መቆሙን ከአካባቢው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ተጎጂዎች ለኢሳት እንደገልጹት አሁን ነገሮች በርደዋል። አከባቢው ተረጋግቷል። ሰላም ነው።
ኢሉባቡር ሁሉም ኢትዮጵያዊ በፍቅርና በመከባበር የሚኖርበት አካባቢ መሆኑን የሚገልጹት ነዋሪዎች በስልጣን ላይ ባለው ስርዓት የሚፈጸመውን የማጋጨትና የማጋደል ሴራ ከእንግዲህ ሁሉም ነቅቶበታል ሲሉም ይናገራሉ።