ኢሳት (ሰኔ 2 ፥ 2009)
ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ቀንድ ያለው የድርቅ አደጋ የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት እንዲሁም የኮሌራ በሽታ ሊስፋፋ እንደሚችል ወርልድ ቪዥን ግብረ ሰናይ ድርጅት አሳስቧል።
በኢትዮጵያ እንዲሁም በጎረቤት ሶማሊያና፣ ደቡብ ሱዳን በመዛመት ላይ ያለው በሽታ ኮሌራ ነው ሲል ድርጅቱ በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
የመንግስት ባለስልጣናትን ጨምሮ በቅርቡ ለአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት የተመረጡት ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም በሽታው ኮሌራ አይደለም ማለታቸው ይታወሳል።
በኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያና ኬንያ ወደ 22 ሚሊዮን አካባቢ የሚጠጉ ሰዎች ለድርቅ አደጋ ተጋልጠው እንደሚገኙ የገለጸው ግብረሰናይ ድርጅቱ፣ በተለይ ህጻናት በምግብ እጥረት ሳቢያ በሽታ የመከላከልና የመቋቋም አቅማቸው ያነሰ በመሆኑ በበሽታው እየተጠቁ መሆኑን አመልክቷል።
በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የእርዳታ ድርጅቶችና ጋዜጠኞች እንዳይንቀሳቀሱ እገዳ በመጣሉ በሽታው እያደረሰ ያለው ጉዳት በአግባቡ አለመታወቁን አክሎ አስታውቋል።
በኢትዮጵያና በሶማሌ ብቻ ከ67ሺ የሚበልጡ ሰዎች ኮሌራ ብሎ በገለጸው በሽታ መጠቃታቸውን ወርልድ ቢዥን በሪፖርቱ አስፍሯል።
በበሽታው ከተያዙት መካከል ወደ 34ሺ የሚጠጉት በኢትዮጵያ መሆኑንም ድርጁቱ አክሎ ገልጿል።
በአጠቃላይ በሁለቱ ሃገራት 1ሺ 400 ሰዎች የሞቱ ሲሆን፣ 769ኞቹ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ግብረ ሰናይ ድርጅቱ አመልክቷል። የአለም ጤና ድርጅት ተመሳሳይ ቁጥር ያለው ሰው በኢትዮጵያ መሞቱን በቅርቡ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።