(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 27/2011) በአፋር ገዋኔ የተነሳው ሕዝባዊ ተቃውሞ ከአዲስ አበባ ወደ ጅቡቲ፣ከጅቡቲ ወደ አዲስ አበባ የሚወስደውን መንገድ በመዝጋት መቀጠሉ ተሰማ።
ወደ መቀሌ የሚጓዙ ተሽከርካሪዎችም እንዳይንቀሳቀሱ መደረጉን ነው ለኢሳት የደረሰው መረጃ የሚያመለክተው።
የራሳችንን ሰላም በራሳችን እናስከብራለን በሚል የተነሱት የአፋር ወጣቶች በንጹሃን ላይ ግድያ የፈጸሙ የመከላከያ አካላት ለህግ የማይቀርቡ ከሆነ መንገዶችን የመዝጋቱ ርምጃ ተጥናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በአፋር ገናሌ የ15 አመቱ ወጣት በመከላከያ ሃይል በግፍ ተደብድቦ በጥይት እንዲገደል መደረጉ የአፋር ህዝብን ቁጣ መቀስቀሱ ነው የተሰማው።
በገናሌ የተጀመረው ህዝባዊ ተቃውሞ ሌሎች አካባቢዎችንም ማዳረሱን ለኢሳት የደረሱት መረጃዎች አመልክተዋል።
በበረሃሌ፣ኮለባ፣አዋሽና ሌሎች ወረዳዎችን በማካተት መቀጠሉን በመግለጽም ጭምር።
የአፋር የሰብአዊ መብቶች ድርጅት ሊቀመንበር አቶ ጋአስ አህመድ እንደሚሉት ህዝባዊ ተቃውሞው ገዳዮች ለህግ ይቅረቡ፣የመከላከያ ሃይሉ በአርቶ አደሩ ላይ የሚያደርሰው ግፍ ይቁም የሚሉና ሌሎች መፈክሮች የተሰሙበት ነው።
እንደ አቶ ጋአስ አባባል ህዝባዊ ተቃውሞው ከአዲስ አበባ ወደ ጅቡቲ፣ከጅቡቲ ወደ አዲስ አባባ የሚወስደውን መንገድ በመዝጋት ተካሂዷል።
ግድያውን የፈጸመው የመከላከያ አባል ለአፋር ፖሊስ ይሰጥ የሚለው ጥያቄም ሌላ ችግርን ፈጥሯል ይላሉ አቶ ጋአስ።የመከላከያ ክፍሉ ጉዳዩን በራሴ አያለሁ እንጂ ለእናንተ አሳልፌ አልሰጥም ማለቱን በመጥቀስ።
በክልሉ ያሉ አመራሮች ለወጣቱ ምላሽ ሰተናል በሚል የሚሰጡት አላግባብ የሆነ አስተያየት ግን ባለፉት 27 አመታት የለመድንው ስለሆነ ባይደግሙት ይሻላል ብለዋል አቶ ጋአስ ።
አፋር ላይ ያለው ሁኔታና እየተሰራ ያለው ተንኮል የለውጥ ሂደቱ ላይ ትልቅ ችግርን ሊያስከትል የሚችል ነው ይላሉ።
እንደ ምክንያትም ለውጡ ኣንዲደናቀፍ የሚፈልጉ አካላት ዋና መጠቀሚያ እያደረጉ ያሉት የአፋር ክልልን መሆኑን በማሳያነት በማቅረብ።
ይህም ሆኖ ይላሉ የለውጥ ሃይሉም ቢሆን መስራት ያለበትን ነገር አለመስራቱ ሂደቱን ቀልድ አስመስሎታል ሲሉም አቶ ጋአስ ያነሳሉ