የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለስኳር ኮርፖሬሽን ብድር እንዲሰጥ መንግስት ጠየቀ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 26/2011) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለስኳር ኮርፖሬሽን ለውጭ ዕዳ መክፈያና ለፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ 13 ቢሊዮን ብር ብድር እንዲሰጥ መንግስት ጠየቀ ።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለስኳር ኮርፖሬሽን ለሚሰጠው ተጨማሪ ብድር መንግሥት ዋስትና እንደሚሰጥም አስታወቋል።

ከሳምንት በፊት በገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢዮብ ተካለኝ ተፈርሞ በዋናነት ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ እንዲሁም በግልባጭ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ  ደብዳቤ መላኩን ሪፖርተር ዘግቧል፡፡

ስኳር ኮርፖሬሽን እየገነባቸው ከሚገኙት የስኳር ፕሮጀክቶች ውስጥ ጣና በለስ ቁጥር አንድና ኦሞ ኩራዝ ቁጥር አንድ የስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቁ በመንግሥት ልዩ አቅጣጫ መሰጠቱን ደብዳቤው ይገልጻል።

ስኳር ኮርፖሬሽን ፕሮጀክቶቹን ለማስፈጸምና ከውጭ ለተበደረው ብድር የወለድ ክፍያ የሚውል ገንዘብ በብድር ንግድ ባንክ ካላገኘ ግዴታውን መወጣት እንደማይችል ታውቋል።

በዚሁም መሰረት  የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመንግሥት ዋስትና  አዲስ ብድር ለኮርፖሬሽኑ እንዲያቀርብ ነው የተጠየቀው ።

ገንዘብ ሚኒስቴር ዋስትና ለመስጠት በጠየቀው መሠረትም ስኳር ኮርፖሬሽን ብድሩን ለማግኘት፣ በአሁኑ ወቅት ከባንኩ ጋር በመነጋገር ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል።

ኮርፖሬሽኑ በገጠመው ከፍተኛ የገንዘብ ቀውስ ምክንያት በአሁኑ ወቅት የስኳር ፋብሪካ ግንባታዎቹ ከሞላ ጎደል መቆማቸው እየተነገረ ይገኛል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ከወራት በፊት ባካሄደው የመስክ ግምገማ፣ የኦሞ ቁጥር አንድና በለስ ቁጥር አንድ ስኳር ፋብሪካ ግንባታዎች መቆማቸውንና ሠራተኞችም እንደተበተኑ አረጋግጧል።

ይኼንንና አጠቃላይ የስኳር ፕሮጀክቶች ችግሮችን በተመለከተ ባለፈው ሳምንት የኮርፖሬሽኑን አመራሮች በመጥራት ቋሚ ኮሚቴው ባካሄደው ስብሰባ፣ ግንባታዎቹን ለማከናወን የሚያስፈልገው ፋይናንስ ሊገኝ ባለመቻሉ ግንባታዎቹ መቆማቸውን ገልጾ ነበር።

ኮርፖሬሽኑ ግዙፍ የስኳር ልማትና የፋብሪካ ግንባታዎችን በሁለት አካባቢዎች ከጀመረ አስር ዓመታት ገደማ ተቆጥሯል።

በኢትዮጵያ ሊገነቡ የታቀዱት 10 ስኳር ፋብሪካዎች ቢጠናቀቁ ኖሮ የሃገሪቱን የስኳር ፍላጎት ከመመለስ በተረፈ ከስኳር ምርት ኤክስፖርት በየዓመቱ 1.2 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ያስገኛሉ የሚል ተስፋ እንደነበር ሪፖርቶች ያመለክታሉ።