በአፋር ክልል በጎርፍ አደጋ በርካታ ዜጎች ጉዳት ደረሰባቸው

ጥቅምት ፬(አራት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ካለፉት ሶስት ቀናት ጀምሮ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ የተነሳ የአዋሽ ወንዝ በመሙላቱ በአሚባራና ዱላሳ ወረዳዎች ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ነዋሪዎች ገለጹ።

ነዋሪዎች እንደሚሉት በአሚባራ አካባቢ ከ5 ሺ ሄክታር በላይ የታረሰ መሬት መውደሙን፣ የ7 ቀበሌ ሰዎች በውሃ መከበባቸውንና ንብረታቸው በውሃ መወሰዱን እንዲሁም አንድ የእርሻ ምርምር ማእከል በውሃ መወሰዱን ገልጸዋል።

እስካሁን የሞቱ ሰዎች መኖራቸውን ለማወቅ በአይቻልም፣ አንዳንድ ነዋሪዎች ግን የሞቱ ሰዎች ይኖሩ ይሆናል ብለው እንደሚገምቱ ገልጸዋል።

በዱላሳ አካባቢ ደግሞ ከ40 ሺ ያላነሰ ህዝብ አደጋ ላይ መውደቁን ነዋሪዎች ገልጸዋል።

የመከላከያ ሰራዊት አባላት በሄሊኮፕተር በመዞር ብስኩት እያደሉ ቢሆንም፣ ነዋሪዎች ግን በመንግስት እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ በቂ በለመሆኑ ወቀሳ አቅርበዋል። ነዋሪዎቹ መንግስት ጀልባ በማቅረብ የሰውን ህይወት ሊታደግ ይገባል ይላሉ።

በጉዳዩ ዙሪያ የክልሉንም መሪዎች ለማናገር የተደረገው ሙከራ አልተሳካም።