ሐምሌ ፲፫ ( አሥራ ሦስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአማራ ክልል ምክር ቤት ለሶስት ቀናት ባካሄደው ስብሰባ ላይ የሃብሩ ወረዳ ተወካይ እንደተናገሩት በሁለቱ ክልሎች መካከል የተነሳው ግጭት እየተባባሰ የሰዎችን ህይወት እየቀጠፈ ነው ። ህጻናት፣ ሴቶችና አዛውንቶች ችግር ላይ መውደቃቸውንም የምክር ቤት አባሏ ገልጸዋል። የክልሉ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ችግሩ በንግግር መፈታቱን ቢናገሩም፣ የአካባቢው ወኪል ግን የሚቀበሉት አልሆኑም።
በሁለቱ ክልሎች መካከል ከአመታት በላይ የሰፈሩት ወታደሮች ለግጭቶች መባባስ ዋና ምክንያት መሆናቸውን ምንጮች ይናገራሉ። በሁለቱ ክልሎች መሪዎች መካከል በተደረገ ስምምነት መሰረት ችግሩ ተፈትቷል ተብሎ በመገናኛ ብዙሃን ከቀረበ በሁዋላ ወዲአውኑ ግጭት ተንስቶ በርካታ ዜጎች ህይወታቻውን ያጡ ሲሆን፣ ግጭቱን በአካባቢው የሰፈሩት ወታደሮች አዛዦች እያባበሱት ነው። ወታደሮቹ አንድ ጊዜ የተወሰኑ የአፋር ተወላጆችን በማነሳሳት፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ የአማራ ተወላጆችን በማነሳሳት ግጭት ይቀስቀሳሉ። የህወሃት የመከላከያ አዛዦች ሁለቱ ክልሎች የሚያደርጉትን ስምምነት የወደዱት አይመስሉም የሚሉት ምንጮች፣ በማንኛውም ጊዜ ሰላም ተፈጠረ ሲባል ግጭት እንደሚያስነሱ ይናገራሉ። ህወሃት በሁለቱ ክልሎች ላይ ያለውን ተጽኖ ይዞ ለመቀጠል፣ በወታደራዊ አዛዦቹ በኩል ግጭት በማስነሳት ህዝቦችን እርስ በርስ ለማበጣበጥ እየሰራ ነው በማለት ምንጮች ይገልጻሉ።
በሌላ በኩል በዚሁ ወረዳ መሬታቸው ለልማት እተባለ የተወሰደባቸው አርሶአደሮች ካሳ ይሰጣችሁዋል ተብለው እስካሁን ምንም አይነት ክፍያ ሊያገኙ ባለመቻላቸው ካለፉት ሁለት አመታት ጀምሮ እያለቀሱ መሆኑን ተወካዩዋ ተናግረዋል።
በተውለደሬ ወረዳም እንዲሁ መሬታቸውን የተቀሙ አርሶአደሮች፣ በተለይም ሴቶች እያለቀሱ መሆኑን የወረዳው ተወካይ ተናግረዋል።