(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 28/2011) በአፋርና ሶማሌ ክልሎች መካከል የተከሰተውን ግጭት በውይይት እንዲፈታ ሁለቱም ወገኖች ጥረት እንዲያደርጉ ተጠየቀ።
የሶማሌ ክልል ካቢኔ ባለፈው ዓርብ ያወጣውን መግለጫ ተከትሎ የተፈጠረው ውዝግብ መካረሩን መረጃዎች ያመለክታሉ።
የተፈጠረውን ግጭት ለማስወገድ በሳምንቱ መጨረሻ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሁለቱንም ወገኖች ማነጋገራቸውን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በሶማሌና አፋር ክልሎች መካከል የከረሩ ቃላት ልውውጡ ወደ ግጭት አምርቶ አካባቢው ዳግም ውጥረት ውስጥ ገብቷል።
ሁለቱም ወገኖች አንዳቸው አንዳቸውን ይከሳሉ።
ለውዝግባቸው መነሻ የሆኑት ደግሞ ሶስት ቀበሌዎች ላይ በኢሳዎችና በአፋሮች መካከል የይገባኛል ጥያቄ መነሳቱ ነው።
የሶማሌ ክልል መንግስት ባለፈው ዓርብ ያወጣውና በሁለቱ ክልሎች መካከል የተደረሰውን ስምምነት የሚያፈርስ መግለጫ መውጣቱ ውጥረቱን አባብሶታል ይላሉ የአፋር የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት ፕሬዝዳንት አቶ ገአስ አህመድ።
የሶማሌ ክልል መንግስት መግለጫ ላይ ሶስቱ ቀበሌዎች በህወሀት ዘመን በእጅ ጥምዘዛ ለአፋር ክልል የተሰጡ ናቸው የሚል አቋም ተይዞበታል።
ለዓመታት በኢሳዎች ላይ በአፋር ልዩ ሃይል የሚፈጸመውን በደል ታግሰን ቆይተናል የሚሉት የሶማሌ ክልል ባለስልጣናት በህገወጥ መንገድ የተደረገውን ስምምነት አንቀበለውም ብለው የልዩ ሃይል ሰራዊታቸውን ወደ አወዛጋቢዎቹ ቀበሌዎች አሰማርተዋል።
ቀበሌዎቹ ቀድሞውኑ የአፋር ናቸው፣ በኢሳዎችና በሌሎች የውጭ ሃይሎች እገዛ የሚፈጸሙት ጥቃቶች እየከፉ በመሆናቸው ርምጃ እወስዳለሁ የሚለው ደግሞ የአፋር ክልል መንግስት ነው።
ይህ ውዝግብ የቆየ ቢሆንም ካለፈው ሳምንት ወዲህ ወደ ለየለት ፍጥጫ ውስጥ ገብቷል።
በዚህም በርካታ ሰዎች ከሁለቱም ወገኖች መገደላቸውን ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት።
ኢሳት ያነጋገራቸው የሁለቱም ወገኖች ምሁራን ጉዳዩን በውይይት መፍታት እንዲቻል ጥሪ አድርገዋል።
ወደ ግጭት የሚወስዱ ማናቸውንም የቃላት ጦርነትና ትንኮሳዎችን በማቆም ለድርድር እድል እንዲሰጡ ምሁራኑና የመብት ተሟጋቾች በመጠየቅ ላይ ናቸው።
የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት የህግ አማካሪ አቶ ጀማል ዲሪዬ ለኢሳት እንደገለጹት በውይይት የማይፈታ ችግር ባለመኖሩ በሶማሌ ክልል መንግስት በኩል ድርድርን ያስቀደመ መፍትሄ ይመረጣል ብለዋል።
የአፋር የሰብዓዊ መብት ድርጅት ፕሬዝዳንት አቶ ገአስ አህመድ በበኩላቸው የሶማሌ ክልል መንግስት ስምምነቱን በመጣስ ለግጭት በር መክፈቱ ተገቢ አይደለም ካሉ በኋላ ውይይት ብቸኛው የመፍትሄ መስመር መሆኑን አመላክተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሁለቱንም ወገኖች ተወካዮች ማነጋገራቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ውይይቱ ለጊዜው ስምምነት ላይ ያልተደረሰበት ቢሆንም በቀጣይ በሚደረጉ ንግግሮች ውዝግቡን ለመፍታት በጠቅላይ ሚኒስትሩ በኩል ጥረት እንደሚደረግ ለማወቅ ተችሏል።