የመንግስት አመራሮች ተፈናቃዮችን ለፖለቲካዊ ፍላጎታቸው ማስፈጸሚያ እየተጠቀሙባቸው መሆኑ ተገለጸ 

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 28/2011) በአንዳንድ ክልሎች የመንግስት አመራሮች ተፈናቃዮችን ለፖለቲካዊ ፍላጎታቸው ማስፈጸሚያ እየተጠቀሙባቸው መሆኑን ፌደራል መንግስቱ አስታወቀ።

በመጠለያ ጣቢያዎች ተፈናቃዮችን እስከማገት የሚደርሱ የክልል አመራሮች መኖራቸውን ባለፈው ዓርብ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት  በቀረበው ሪፖርት ላይ  ተመልክቷል።

የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል የትኛውንም ዋጋ ከፍለን የዜጎችን ስቃይ ለማስቆም ወስነናል ብለዋል።

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ዓርብ እለት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመንግስት ተቋቁሞ ወደተለያዩ አካባቢዎች የተሰማራን ግብረ ሃይል ሪፖርት አዳምጧል።

ሪፖርቱ በሀገሪቱ የሚታየውን ግጭትና መፈናቀል የተመለከተ ዝርዝር መረጃዎችን የያዘ መሆኑ ተገልጿል።

በሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል የቀረበው ሪፖርት ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ከዳር እስከዳር ህዝብን አደጋ ውስጥ ከከተቱ ግጭቶችና መፈናቀሎች ጀርባ ዋንኞቹ ተዋናዮች የመንግስት ሃላፊዎች መሆናቸውን መግለጻቸው አነጋጋሪ ሆኗል።

ወይዘሮ ሙፈሪያት በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ የፖለቲካ አመራሮች የችግሮቹ ጠንሳሽና አቀጣጣይ፣ እንዲሁም እንዳይፈታ እክል በመፍጠር በዋነኝነት ተሳታፊ በመሆናቸው ችግሩን በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍታትም ሆነ ማስቆም እንዳልተቻለ ገልጸዋል።

አንዳንድ የክልል አመራሮች ፖለቲካዊ ፍላጎታቸው እንዲፈጸምላቸው ጫና ለመፍጠርና ለማስገደድ ተፈናቃዮችን በመጠለያ ጣቢያዎች እስከ ማገት የደረሰ ተግባር እየፈጸሙ እንደሚገኙ ነው የሰላም ሚኒስትሯ ለፓርላማ የገለጹት።

አንዳንድ አካባቢ የፖለቲካ አመራሩ ራሱ ገዳይ ወይም አስገዳይ ሆኖ በሌላ በኩል ደግሞ የመብት ተቆርቋሪ ሆኖ ይቀርባል ያሉት ሚኒስትሯ፣ እነዚህን ኃይሎች በሕግ ቁጥጥር ሥር ማዋል ካልተቻለ ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬአቸው መመለስ እንደማይቻል ጠቁመዋል።

መንግስት ታግሷል ከዛሬ ነገ ይሻሻላል በሚል በትዕግስት ቆይቷል አሁን ግን ርምጃ መውሰድ እንጀምራለን ብለዋል ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል።

”ጨከን ማለትና መከፈል ያለበት ዋጋ ተከፍሎ የዜጎችን ስቃይ ለማስቆም ወስነናል” ሲሉም በፓርላማ ተገኝተው የመንግስትን ውሳኔ አስታውቀዋል።

በዓርቡ የፓርላም ስብሰባ ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንም የመንግስት መዋቅር የችግሮች ሁሉ ምንጭ መሆኑን በመግለጽ መንግስት ቁርጠኛ ሆኖ ርምጃ መውሰድ ይጀምራል ብለዋል።

”ዜጎች ይፈናቀላሉ፣ ይሞታሉ፣ አመራሮች ግን አይሞቱም፣ አይፈናቀሉም ያሉት አቶ ደመቀ፣ ”ነገሩ በደሃ ኢትዮጵያውያን ላይ ጨዋታ ሆኗል” ሲሉ ገልጸዋል፡፡

”በብሔር ጉያ ውስጥ መደበቅ በየትኛውም ሚዛን አመራር እንደማያሰኝም ነው የተናገሩት ”ስለዚህ ወደ ሰንኮፉ መጠጋትና መንቀል ያስፈልጋል” ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን።