በአገሪቱ ያሉ የደህንነት ሰራተኞች ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው

ግንቦት ፲፭ ( አሥራ አምስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ሚያዚያ ወር መጀመሪያ ላይ በአገሪቱ የሚገኙ ዋና ዋና የደህንት አባላት ድሬዳዋ ውስጥ ለ9 ቀናት የቆየ የማጣሪያና የመለያ ስብሰባ አካሂደዋል። በስብሰባው ላይ የህወሃት አባል ያልሆኑ የሌሎች ብሄር ተወላጆች፣ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የደህንነት አባላትን ለጠላት አጋልጠው በመስጠት ህይወታቸው እንዲያልፍ እያደረጉ ነው በሚል ከፍተኛ ወቀሳ ደርሶባቸዋል። የደህንነት አባላቱ ለስርዓቱ ታማኝ ያልሆኑ ባልደረቦቻቸውን አጋልጠው እንዲሰጡ ማስጠንቀቂያ አዘል ማስፈራሪያ ተሰጥቷቸዋል። የደህንነት አባላት በተለያዩ ምድቦች ተከፋፍለው እርስ በርስ እንዲገማገሙ መደረጉን የገለጹት የኢሳት ምንጮች፣ በተለይም ድሬዳዋ እና ጅጅጋ ላይ ባልታወቀ ምክንያት የተገደሉትን ሁለት የጸረ ሽብር ግብረሃይል የደህንነት አባላትን መረጃ እንዲያወጡ ሲጨናነቁ ሰንብተዋል። ባለፈው አንድ አመት ከ6 ያላነሱ የደህንነት አባላት ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ የደህንነት ባለስልጣናት ግድያውን የሚፈጽሙት የራሳችን የደህንነት አባላት ናቸው ብለው እንደተናገሩና በስብሰባው ላይ የተገኙት የደህንነት አባላቱ የሚጠረጥሩዋቸውን ሰዎች እንዲጠቁሙ ተጠይቀዋል።
የኢሳት ምንጮች እንደሚሉት ግን ግድያው በመከላከያ የደህንነት አባላትና በመደበኛው የደህንነት አባላት መካከል ሳይፈጸም እንዳልቀረ ይገልጻሉ። በቅርቡ የተገደሉት ሁለቱ የጸረ ሽብር ግብርሃይል የደህንነት አባላት፣ በመከላከያ የደህንነት አባላት ተገድለዋል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
አንድ የደህንነት ባለስልጣን በስብሰባው ላይ “እንዲህ አይነቱ ግድያ የሚፈጸመው አስመራ ባሉ ተቃዋሚዎች ሳይሆን በእኛው አባላት ነው” ያሉ ሲሆን፣ እንዲህ አይነቱን ግድያ እና ስርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ነገር እንዲፈጠር አንፈቅድም በማለት በሃይለቃል መናገራቸውን ምንጮች ገልጸዋል።
በአቶ ጌታቸው አሰፋ የሚመራው የደህንነት ተቋም፣ ከመከላከያ የደህንነት ተቋም ጋር የፈጠረው አለመግባባት እርስ በርስ እየተፈራሩ እንዲኖሩ እንዳደረጋቸው ምንጮች ገልጸዋል። የዋናው የደህንነት መስሪያ ቤቱ ስብሰባ ከጠራህ በሁዋላ፣ ስብሰባውን ሳትጨርስ በተለያዩ መንገዶች የምትገደልበት ሁኔታ እየተፈጠረ በመሆኑ፣ በጋራ ሆኖ ስብሰባ ማካሄድ እየቸገረ ነው የሚሉት እነዚህ ምንጮች፣ አብዛኞቹ የሚገደሉት ከዋናው ደህንነት ሰራተኞች በመሆኑ፣ ገዳዮቹ የመከላከያ የደህንነት አባላት ናቸው ብለው እንዲያምኑ እንዳደረጋቸው ይገልጻሉ። “በደህንነት አባላቱ ውስጥ የተፈጠረውን ችግር ለመቅረፍ ሙከራ ከማድረግ ይልቅ ችግሩን ከብሄር ጋር አያይዞ ለማቅረብ መሞከር ራስን ማታለል ነው፣ ችግሩ የራሳቸው የውስጥ ችግር በመሆኑ መፍትሄውንም መፈለግ ያለባቸው ራሳቸው ናቸው” ሲሉ ያክላሉ።