ታኀሳስ ፳፩(ሃያ አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ኢህአዴግ ከመላው አገሪቱ ለተውጣጡ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች መጪውን ምርጫ በተመለከተ ስልጠና እየሰጠ ሲሆን፣ ከስልጠናው በፊት ማንኛውም ባለስልጣን ስልክ ይዞ መግባት እንደማይችል ጥብቅ የሆነ መልእክት በመተላለፉ፣ ሁሉም ባለስልጣናት ስልካቸውን መኪናቸው ውስጥ እየተዉ ወይም ለሹፌሮቻቸው እየሰጡ መግባታቸው ታውቋል።
ወደ ስብሰባው የሚገባ ሰው ማንኛውንም አይነት የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን መያዙንና አለመያዙን ለማረጋገጥ ጥብቅ ፍተሻ እንደሚካሄድበት የክልሉ ዘጋቢያችን ገልጿል። በገልማ አባ ገዳ አዳራሽ በሚካሄደው ስብሰባ ሚኒስትሮች፣ የሁሉም የክልልና ከተማ አስተዳደር መስተዳድሮችና ከዞን ጀምሮ ያሉ የስራ አመራሮችና የድርጅቱ ዋና ዋና ካድሬዎች ተገኝተዋል።
ተሰብሳቢዎቹ ምንም አይነት ሞባይል ስልክ ወደ አዳራሽ ይዘው እንዳይገቡ መከልከላቸው ከዋናው አጀንዳው ይልቅ መነጋገሪያ መሆኑን የሚገልጹት ምንጮች፣ ትእዛዙ የተላለፈውም የኢህአዴግ ስብሰባዎች እየተቀረጹ በመገናኛ ብዙሃን መቅረባቸው የድርጅቱን አመራሮች እያበሳጨ በመምጣቱ ነው።