(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 24/2011) በትግራይ አዲግራት ከተማ በርካታ መኖሪያ ቤቶች መፍረሳቸው ቁጣን አስነሳ።
ክልሉን የሚያስተዳድረው ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ህገወጥ ናቸው በሚል ከ70 በላይ መኖሪያ ቤቶችን ማፍረሱ ታውቋል።
ተጨማሪ መኖሪያ ቤቶችም ሊፈርሱ እንደሚችሉ ነዋሪዎች ገልጸዋል። በትግራይ የእንደርታ ተወላጆች ላይ የክልሉ መንግስት በደል እየፈጸመ ነው በሚል ተቃውሞ ተነስቷል።
በመቀሌ ባለፈው ሳምንት በእንደርታና በመቀሌ እግርኳስ ቡድን ደጋፊዎች መሃል በተፈጠረ ግጭት በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ የሚታወስ ነው።
የትግራይ ክልላዊ መንግስት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካዔል ሰሞኑን ተናገሩ የተባለው ለእንደርታ ተወላጆች ተቃውሞ መባባስ ምክንያት እንደሆነ ይነገራል።
ዶክተር ደብረጺዮን በእንደርታ የተጀመረውን የመብት ጥያቄ ተከትሎ ጥያቄው የባንዳዎችና የተላላኪዎች ነው የሚል ምላሽ መስጠታቸው በትግራይ ክልል ቁጣን ቀስቅሷል።
የእንደርታ ህዝብ በሚኖርበት የአዲግራት አከባቢ ቀደም ሲል ጀምሮ የመብት ጥያቄ ይነሳ እንደነበረ የሚገልጹት ምንጮች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጥያቄው ምላሽ እንዲያገኝ የተጀመረው እንቅስቃሴ ለህወሀት ስጋት መፍጠሩ እየተነገረ ነው።
የዶክተር ደብረጺዮን የሰሞኑ አስተያየት የእንደርታን ህዝብ ይበልጥ ለተቃውሞ ማስነሳቱን ነው የደረሰን መረጃ የሚያመላክተው።
ህወሃት በትግራይ የተለያዩ ማህብረሰቦች መሃል ክፍፍልን በመፍጠር አንዱን ዝቅ ሌላው ከፍ የሚያደርግ ፖሊስ ይከተላል በሚል ለዓመታት ውስጥ ለውስጥ ቅሬታ ሲፈጥር የዘለቀው ጉዳይ አደባባይ መውጣት ጀምሯል የሚሉት የኢሳት ምንጮች የህወሀትን ህልውና አደጋ ውስጥ የሚከት እንደሆነም ገልጸዋል።
የሰሞኑ የዶክተር ደብረጺዮን አስተያየት በህወሀት ሌሎች መሪዎች ዘንድ ተቃውሞ ማስነሳቱም ታውቋል።
የህወሀት ቃለቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ለህዝብ ተገቢውን ምላሽ መስጠት ሲገባ ፍረጃ ትክክለኛ ውሳኔ አይደለም ሲሉ ድምጻቸው አሰምተዋል።
የአረና ፓርቲ አመራሮችም ዶክተር ደብረጺዮን የተናገሩትን የትግራይን ህዝብ የሚከፋፍል አደገኛ አቋም ሲሉ ተቃውሞአቸውን በማሰማት ላይ ናቸው።
ከትላንት ጀምሮ በአዲግራት መኖሪያ ቤቶችን የማፍረሱ እንቅስቃሴም የህወሀት አገዛዝ በእንደርታ ህዝብ ላይ የጀመረው የበቀል እርምጃ አንዱ አካል እንደሆነ ምንጮች ይገልጻሉ።
በአዲግራት ከ70 በላይ መኖሪያ ቤቶችን በማፍረስ ለእንደርታ ህዝብ ያለውን ንቀት አሳይቷል የሚሉት የአዲግራት ነዋሪዎች ህዝቡ ወደከፍተኛ ተቃውሞ ሊሸጋገር እንደሚችል ገልጸዋል።
የህወሃትን ስልጣን በበላይነት በተቆጣጠሩ የአንድ አከባቢ ሰዎች የተነሳ እንደርታ ህዝብ ላይ አድሎና መገለል እንደሚፈጸም የሚገልጹት ነዋሪዎች ህዝቡ ያነሳውን የመብት ጥያቄ ለመቀልበስ ህወሀት የበቀል አምጃውን መጀመሩን ተናግረዋል።
የመኖሪያ ቤቶችን በህገወጥ ስም የማፍረሱ እርምጃ የእንደርታዎችን እንቅስቃሴ ለማስቆም እንደሆነም ይገልጻሉ።
የአዲግራት ከተማ አስተዳደር የቤቶች ማፍረሱ ርምጃ ከህገወጥነት ጋር የተያያዘ መሆኑን በመጥቀስ ተጨማሪ ቤቶችን ለማፍረስ ማቀዱን አስታውቋል።
በእንደርታ ህዝብ የተጀመረው የመብት ትግል እንቅስቃሴን ተከትሎ በቅርቡ በመቀሌ የተካሄደው የእግር ኳስ ጨዋታ በሰው ህይወት ላይ ጉዳት በማድረስ መቋረጡ የሚታወስ ነው።