በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በተነሳ ግጭት ተማሪዎች ተጎዱ

ታህሳስ  ፳፮(ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሳይንስ ፋኩልቲ እየተባለ በሚጠራው ግቢ ትናንት ምሽት ተጀምሮ ዛሬ ከጧቱ 3 አሰት ላይ በድጋሜ በተፈጠረ የብሄር ግጭት በርካታ ተማሪዎች በመጎዳታቸው በአምቡላንስ ወደ የካቲት 12 ሆስፒታል ተወስደዋል።

ግጭቱ በመካረሩ ከሰአት በፊት ከአራት ኪሎ ወደ ስድስት ኪሎ የሚወስደው መንገድ ተዘግቶ ነበር። የዩኒቨርስቲው ጠባቂዎች ግጭቱን መቆጣጠር ባለ  መቻላቸው ሙሉ የድንጋይ መከላከያ የለበሱ  የፌደራል ፖሊስ አባላት ወደ ዩኒቨርስቲው በመግባት ተማሪዎችን ደብድበዋል።

ከግቢው አምልጦ መውጣት የቻለ አንድ የምህንድስና ክፍል  የመጀመሪያ አመት ተማሪ ለዘጋቢያችን እንደተናገረው በሁለቱ ብሄር ማለትም በኦሮሞና በትግራይ ተማሪዎች መካከል የተጀመረው ግጭት የተፈጠረው ትላንት ማታ ከምሽቱ 3 ሰአት ሲሆን በተወሰነ መንገድ ግጭቱ በቁጥጥር ስር ቢውልም ዛሬ ጧት አገርሽቶ በድንጋይ ከመወራወር ጀምሮ በዱላ እስከ መደባደብ መድረሱን ተናግሯል።

ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ተማሪዎች ከቀላል እስከ ከባድ የሚደርስ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፣ የመማሪያ ክፍሎች መስታውቶችም ተሰባብረዋል።

ተማሪዎች በመልክ፣  በልዩ የብሄር ምልክት እና በስም ጭምር ተፈላልገው ወደ ጸብ የገቡበት ምክንያት የትግራይ ብሄር ተማሪዎች የኦሮሚያን ብሄር ተወላጆችን የሚያንቋሸሹ ንግግር አድርገዋል፣ ጽሁፎችንም በግቢው ውስጥ ለጥፈዋል በሚል ስሜት ነው።

የፌደራል ፖሊስ ልዩ ኮምናዶ የትግራይና እና የኦሮሚያ ብሄር ተማሪዎችን ለይተው ማንበርከከካቸውን ፣ ግጭቱ ወደ ስድስት ኪሎ ዩኒቨርስቲ እንዳይዛመት አካባቢውን ዘግተው እንደነበር ዘጋቢያችን ገልጿል።

በአራት ኪሎ አካባቢ የሚያልፉ ሰዎች መታወቂያቸው እየታየ አንዳንዶች ደግሞ ሲደበደቡ እንደነበር ታውቋል። ቁስለኞችን የያዙ በርካታ አምቡላንስ መኪኖችም ተማሪዎችን ወደ የካቲት 12 ሆስፒታል ሲያመላልሱ ታይተዋል።

የፌደራል ፖሊስ አባላት ተማሪዎችን በፒክ አፕ መኪኖች እየጫኑ  ወደ ወረዳ 14 ፖሊስ ጣቢያ ወስደዋቸዋል።

ትናንት ሌሊት ከተያዙት ተማሪዎች መካከል ብስራት አሽኔ ፣ ዘላለም ደምሴ፣ ቢኒያም ተክሉ፣ ሳራ እስጢፋኖስ፣ መዝሙር የኔአምላክ፣ ሰናይት ቢረጋ፣ ሞገስ በላይነህ፣ ህልና ንጉሴ እና አንዋር ጃፋ ይገኙበታል።

ዛሬ የተወሰዱትን ተማሪዎች ስም ዝርዝር ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ዛሬ ሞሶቦ ኢትዮጵያ ለአንድነት የተማሪዎች ንቅናቄ የሚል ማህበር መመስረታቸውን የተማሪዎች ተወካይ ለኢሳት ገልጿል።

ተወካዩ ወዲ ለሜሳ እንደገለጸው ከንቅናቄው አላማዎች መካካል ያልምንም ቅድመ ሁኔታ ሰላማዊ የፖለቲካ ታጋዮች እና ሰላማዊ ጋዜጠኞች እንዲፈቱ፣ ብሄራዊ እርቅ በአስቸኳይ እና በአፋጠኝ በአገሪቱ ላይ እንዲደረግ የሚሉት ይገኙበታል።

ተወካዩ እንደሚለው ጥያቄያቸውን ለመንግስት በማቅርብ መልስ እንዲሰጥ ከመጠየቅ ጀምሮ ረሀብ አድማ ፣ ትምህርት ማቆም እና ሰላማዊ ሰልፍ እስከ ማዘጋጀት የሚደርስ እርምጃ ለመውሰድ አቅደዋል።