ታህሳስ 23 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት:- የኢሳት የአዲስ አበባ ዘጋቢ እንደገለጠው፣ የመጽሀፍ አዙዋሪዎች የአቶ በረከትን አዲሱን “የሁለት ምርጫዎች ወግ” መጽሀፍ በተጽእኖ እንዲሸጡ ቢደረግም፣ ከመጽሀፉ ሽያጭ ያገኙት ትርፍ ስድብና ውግዘት ብቻ ነው።
ዘጋቢያችን “አንዱን የመጽሀፍ አዟሪ ” በቀን ውስጥ ስንት የአቶ በረከትን መጽሀፎች ትሸጣለህ?” ብሎ ሲጠይቀው፣ ” በቀን ውስጥ ስንት ስድቦችን አተረፍክ?” ብለህ ብትጠይቀኝ ይሻለኛል” ብሎ እንደመለሰት ገልጧል።
ዘጋቢያችን እንደሚለው የአዲስ አበባ ህዝብ የአቶ በረከትን መጽሀፍ ገዝቶ ሊያነብ ቀርቶ በረከት ያለበትን ማንኛውንም ነገር ማየት አይፈልግም።
የአቶ በረከትን መጽሀፍ በግዳጅ እንዲሸጥ የታዘዘ አንድ በፒያሳ አካባቢ የሚገኝ አዙዋሪ በበኩሉ፣ “ነዋሪውን የአቶ በረከትን መጽሀፍ ግዛን ብለን ስንጠይቀው አንዳንዱ ይሰድበናል፣ ሌላው ደግሞ በአይኑ ገላምጦን ያልፋል” ሲል ተናግሯል።
በምርጫ 97 ወቅት የአቶ በረከት ፎቶ ግራፍ በጋዜጦች የፊት ገጽ ላይ ከተቀመጠ ፣ የጋዜጣ አከፋፋዮችና አዟሪዎች ጋዜጦችን አንሸጥም ይሉ እንደነበር ይታወሳል።
አቶ በረከት የሁለት ምርጫዎች ወግ የተባለውን መጽሀፋቸውን በሼክ ሙሀመድ አላሙዲን ስፖንሰርነት ማሳተማቸው ይታወሳል።