የአቦሬ ገበያን ቃጠሎ ተከትሎ፣ በአካባቢው ኗሪ የነበሩ ሰዎች ጐዳና መውደቃቸውንና የወረዳ ስድስት አስተዳደርም ሕገወጥ ናችሁ በማለት ጊዜያዊ መጠለያ እንዳያገኙ ማድረጉን ተዘገበ

ታህሳስ 23 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት:- በየካ ክፍለ ከተማ በሚገኘው የአዋሬ ገበያ ከሁለት ሳምንት በፊት በተነሳ ቃጠሎ በርካታ የንግድ ቤቶችና መኖሪያዎች መውደማቸውን ተከትሎ፣ በአካባቢው ኗሪ የነበሩ ሰዎች ጐዳና መውደቃቸውንና የወረዳ ስድስት አስተዳደርም ሕገወጥ ናችሁ በማለት ጊዜያዊ መጠለያ እንዳያገኙ ማድረጉን ሪፖርተር ዘገበ
ላለፉት 22 ዓመታት በአዋሬ ገበያ አካባቢ እንደኖረችና ተወልዳ ያደገችው እዚያው የወደመው ሠፈር ውስጥ እንደነበር የተናገረችው ወጣት ገበያነሽ ለማ፣ የእሷን ቤተሰቦች ቤት ጨምሮ 32 መኖሪያ ቤቶች በቃጠሎ መውደማቸውን፣ ሆኖም ወረዳው የገበያ ማዕከል እንጂ መኖርያ ቤት እንደማያውቅ በመግለጽ ‹‹ሕገወጥ ናችሁ›› በማለት ምንም ዓይነት ድጋፍ ሊሰጣቸው እንዳልቻለ ለሪፖርተር ገልጻለች፡፡

“ከአቅማችን በላይ በመሆኑ የንግድ ቤት እንጂ መኖርያ ቤት ልንሰጣችሁ አንችልም፡፡ ንግድ ቤቶችን እንጂ መኖርያ ቤቶችን አናውቅም፡፡ ከዚህ በፊት መኖርያ ቤት ስለመኖሩ ወረዳው የሚያውቀው ነገር የለም፤” መባላቸውን የገለጸችው ገበያነሽ፣ ከዚህ ይልቅ በንግድ ስም ብትደራጁ ሱቅ ይሰጣችኋል ቢላቸውም፣ አቅማቸው እንደማይፈቅድ ለወረዳው ማስታወቃቸውን ገልጻለች፡፡
በብድርና ቁጠባ እንዲደራጁ መፍትሔ መቅረቡን ነገር ግን በጊዜያዊ መጠለያነት ቀይ መስቀል ሊሰጣቸው የነበረውን ድንኳን መከልከሉንም ወጣቷ ተናግራለች፡፡ “ለቀይ መስቀሎች ሰዎቹን አናውቃቸውም፤ ሕገወጦች ስለሆኑ ድንኳን አይሰጣቸውም ብሎ መለሳቸው፤” ስትል አክላለች
በአካባቢው ባለፈው ረቡዕ ከመንገድ ዳር የተኙ ሕመምተኛ አዛውንትን ጨምሮ በርካታ ሴቶች፣ የሚጠቡ ሕፃናትንና አረጋውያንን ለዕለት ጉርስ ሳንቲም ከመንገደኛው ሲለምኑ ለማየት ተችሏል፡፡
ከዚህ ቀደም ሕገወጥ ናችሁ ከዚህ አካባቢ እንድትነሱ የሚል አንድም ማስጠንቀቂያ ያልሰጣቸው መሆኑን የምትናገረው ገበያነሽ፣ ነዋሪዎቹ በተደጋጋሚ ለወረዳው የሕጋዊነት ጥያቄ ቢያቀርቡም ምላሽ ሳይሰጣቸው መቆየቱን ገልጻለች፡፡
የቃጠሎውን አጋጣሚ ተጠቅመው ሕገወጦች ብለውናል ብትልም መኖሪያ ቤቶቹ ኪራይ እንደማይከፈልባቸው አልሸሸገችም፡፡ ሆኖም ቤቶቹ ተለክተው ኪራይ እንዲከፍሉ ወረዳውን ጠይቀው ምላሽ እንዳልሰጣቸው ገልጣለች።
ሪፖርተር ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች “እንደ ዜጋ ሰብዓዊ ድጋፍ ሊደረግልን ይገባል፤ መጠለያ እንዴት እንከለከላለን?” በማለት የታመሙ ቤተሰቦቻቸውን መንገድ ላይ ለማስታመም መገደዳቸውን ከእንባ ጋር በምሬት ገልጸዋል፡፡
በየካ ክፍለ ከተማ የወረዳ ስድስት ሥራ አስፈጻሚ አቶ አሉላ ገብረ ኪዳን ‹‹አንድም መኖርያ የሚባል ቤት የለም፡፡ በላስቲክ ቤት ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ያንን እያሻሻሉ መኖር ከመጀመራቸው በቀር ሕጋዊ መኖርያ ቤት የለም፤›› ብለዋል።
ሕጋዊ ሆነው የሚኖሩ ሰዎችን አላገኘንም ያሉት ሥራ አስፈጻሚው፣ የቀበሌ ቤት ለመሆናቸው የሚያረጋግጡ፣ ግብር የሚከፈልባቸው ደረሰኞች፣ መታወቂያና ሌላም ሰነድ ተጠይቀው ሊያቀርቡ አልቻሉም በማለት ነዋሪዎች ‹‹ዝም ብለው›› ይኖሩ እንደነበር ሰብስበው ባወያዩዋቸው ወቅት እንዳመኑላቸው ተከራክረዋል፡፡ ‹‹በዚህ ሁኔታ ሕጋዊ ቤት መስጠት ያስቸግረናል፤›› ያሉት አቶ አሉላ፣ አዋሬ ገበያ ውስጥ ምንም ዓይነት መኖርያ ቤት እንደሌለ አስረድተዋል፡፡
ቀይ መስቀል ድንኳን ለመስጠት ሞክሮ ተከልክሏል ለሚለው የኗሪዎቹ ቅሬታ ኃላፊው ሲናገሩ፣ ‹‹ድንኳኑን በቋሚነት መጠቀም አይቻልም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹እነኚህ ሰዎች ከድንኳን ይልቅ በአካባቢው ካሉ ጐረቤቶቻቸው ተጠግተው ቢኖሩ ነው ትክክል የሚሆነው፤›› ካሉ በኋላ፣ ድንኳን ማቆሙ መፍትሔ አይሆንም ብለዋል፡፡ ‹‹ሕጋዊ ያልሆነውን ነዋሪ ድንኳን ውስጥ ማስቀመጥ ነገ ሕጋዊ ቤት መስጠት ስለሚያስከትል መሠረታዊ መፍትሔ አይሆንም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ባይቃጠልባቸው ኖሮስ?” በማለት ከሪፖርትር ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ አሉላ፣ አካባቢው በመልሶ ማልማት ፈራሽ ስለሆነ በዳግም ምዝገባ ቤት ለቤት እየተዞረ የሚመዘገብ በመሆኑ ማን ሕጋዊ ሆኖ መመዝገብ እንዳለበት ያኔ ይለይ ነበር ካሉ በኋላ፣ እስካሁን ሕገወጥ ሆነው ሲኖሩ ዕርምጃ አለመወሰዱ ችግር ቢሆንም፣ ችግሩ በታየበት ወቅት መታረም አለበት ይላሉ፡፡ ‹‹አሥር ዓመት የሸፈተ ሽፍታ ሳትነቃበት ያን ሁሉ ጊዜ ሊቆይ ይችላል፡፡ መጨረሻ ላይ ግን አሥረኛው ዓመት ላይ ስለያዝኩት ተብሎ ወደኋላ መመለስ ሳይሆን በተያዘበት መታረም አለበት፤” በማለት የቃጠሎውን መከሰት ከወረዳው የሕጋዊነት ፍላጐት ጋር አያይዘውታል፡፡

መንገድ ላይ የተገኙትን ሰዎች በይፋ ሕጋዊ አይደላችሁም ብሎ መሸኘት እስኪቻል ድረስ ለምን ጊዜያዊ መጠለያ አይሰጣቸውም ተብለው የተጠየቁት አቶ አሉላ፣ በአካባቢው የሚኖሩት ድሮ የነበሩ ሰዎች ሳይሆኑ በየጊዜው አዳዲስ ሰዎች እየመጡ፣ በተለይ ኑሯቸው ዝቅተኛ የሆኑት በዝቅተኛ ኪራይ የሚኖሩበት አካባቢ እንደሆነ ገልጸው፣ ወረዳው ለተቸገሩት ሰዎች የምግብና የዕለት ደራሽ ዕርዳታ በመስጠት ጊዜያዊ መፍትሔ መስጠት እንደቻለ ተናግረዋል፡፡
“ድንኳን መጥቶ አልመለስንም፣ መፍትሔም አይሆንም፡፡ ነገር ግን የሰዎቹ ፍላጐት በአጋጣሚው ቤት ለማግኘት እንጂ አንድም ሰው መንገድ ላይ እንዳላደረ አረጋግጠናል፤” ያሉት አቶ አሉላ፣ ማንም ሰው ቀዳዳ ካገኘ ቤት ለማግኘት የማይጥር የለም በማለት የነዋሪዎቹ ፍላጐት ጊዜያዊ መጠለያ ለማግኘት እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

የቃጠሎው ሰበብ መንገድ ላይ ያወጣቸው አቅመ ደካሞች፣ ሴቶችና ሕፃናት እንዲሁም ታማሚዎች ግን የመጠለያ ያለህ በማለት የሰብዓዊነትና የዜግነት ጥያቄ አድርገውታል ሲል ጋዜጣው ዘግቧል።