በአዲስ አበባ የሚኖሩ ነዋሪዎች ቤቶቻችን ሆን ተብሎ በመንግስት ሰዎች እየተቃጠሉብን ነው አሉ

መጋቢት ፳፮ (ሀያ ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በአዲስ አበባ በትናንትናው እለት ብቻ ሁለት ቦታዎች ላይ በተመሳሳይ ሰአት ቃጠሎ የደረሰ ሲሆን፣ ድርጊቱ ያበሳጫቸው ወጣቶች ከፌደራል ፖሊስ አባላት ጋር መጋጨታቸውን የአይን እማኞች ተናግረዋል።
የመጀመሪያው የእሳት አደጋ የደረሰው በአባኮራን ሰፈር ፋሲል ሆቴል አጠገብ ከቀኑ 5፡10 ሲሆን፣ ቃጠሎውም እሰከ 7፡30 ድረስ መቆየቱ ታውቋል። አንድ ሰው ጭንቃላቱ አካባቢ ቃጠሎ ሲደርስበት ሌላ አንዲት ወጣት ደግሞ ሰውነቷ ተቃጥሎአል። ከ40 በላይ ቤቶች እና ብዙ ንብረትም መውደሙን የአይን እማኞች ገልጸዋል።
የእሳት አደጋ መኪኖች ከ45 ደቂቃ በሁዋላ የደረሱ ሲሆን፣ ከቦታው ከደረሱም በሁዋላ ውሀ የለንም በማለታቸው ከአካባቢው ወጣቶች ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞአቸዋል። ከወጣቶች ጋር በተፈጠረ ግጭት አንድ የእሳትና ድንገተኛ አደጋ መኪና በድንጋይ የተሰበረ ሲሆን፣ የመኪናው ሾፌርም ተደብድቧል። የፌደራል ፖሊስ ወደ አካባቢው በመድረስ በወጣቶች ላይ ድብደባ የፈጸመ ሲሆን፣ 3 ሰዎችም ተይዘው ታስረዋል። አንድ የእሳት አደጋ ሰራተኛ ነፍስ ማዳኑን ትቶ ፣ ገንዘብ ሲሰበስብ እጅ ከፍንጅ መያዙም ታውቋል። የአካባቢው ሰዎች ቤታቸውን ያቃጠለባቸው መንግስት መሆኑን ይናገራሉ።
በዚሁ እለት በተመሳሳይ ሰአት አውቶቡስ ተራ አካባቢ 32 ቀበሌ ላይ የሚገኙ ቤቶች ለሁለተኛ ጊዜ ተቃጥለዋል። በዚህ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ነዋሪዎች ቀደም ብሎ አካባቢውን እንዲለቁ ተነግሮአቸው የነበረ ቢሆንም ነዋሪዎቹ ለመልቀቅ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተው ነበር። ከሁለት ሳምንት በፊት በዚህ አካባቢ በደረሰው የእሳት አደጋ 11 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል። የመንግስት መገናኛ ብዙሀን የሟቾች ቁጥር 8 መሆኑን መዘገባቸው ይታወሳል። ትናንት በተነሳው ቃጠሎ ጊዚያዊ መጠለያ በመስራት ተጠልለው የነበሩት ሰዎች መጠለያቸው ሙሉ በሙሉ እንደወደመባቸው ታውቋል።
ነዋሪዎች መንግስት ተለዋጭ ቤት ሳይሰጠን ቤታችንን ለቀን አንወጣም በማለት ለረጅም ጊዜ ሲያንገራግሩ ቆይተዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ የእሳት አደጋ ባለስልጣናትን አስተያየት ለማካተት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።