በአዲስ አበባ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 09 እና 10  ውስጥ ከሀይለስላሴ ዘመን አንስቶ በካምፕ ሲኖሩ የነበሩ  ከ500 በላይ አባት ጡረተኞችና አርበኞች  ቤታቸው  እንዲፈርስ በመደረጉከነቤተሰቦቻቸው ሜዳ ላይ መበተናቸውን ለኢሳት ገለጹ።

ጥር ፯(ሰባት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ልኳንዳ  ተብሎ በሚጠራው አካባቢ  የሚገኘውንና ከጥንት ጀምሮ  የአባት ጦረኞችና የአርበኞች መኖሪያ የሆነውን የወታደር ካምፕ  ቦታው ተከልሎላቸው የሰሩት  ራሳቸው   አርበኞቹ  መሆናቸው ተመልክቷል።

ፈጽሞ ባላሰቡበትና ባልተዘጋጁበት ሁኔታ መኖሪያ ካምፓቸው ያለ ምንም ተለዋጪ ማረፊያ  መሳሪያ በታጠቁ ወታደሮች እንዲፈርስ መደረጉ እንዳስደነገጣቸው የሚናገሩት ነዋሪዎቹ፤ ውሳኔውን በመቃወም እስከ ፍትህ ሚኒስቴር ድረስ አቤት ቢሉም ሰሚ ማጣታቸውን ገልጸዋል።

እንደ ነዋሪዎቹ  ገለጻ፦ቤታቸው ፈርሱ ሜዳ ላይ ከተበተኑትና የላስቲክ ድንኳን ሰርተው ከተጠለሉት ነዋሪዎች መካከል የኤች አይ ቪ/ ኤድስ ህመምተኞችና  በርካታ ህጻናት ይገኙበታል።

የአካባቢው መስተዳድር አካላት ነዋሪውን ሊያነጋግሩ ሲመጡ ወጣቶቹ ልጆች ባንዲራ  እያውለበለቡ  አባቶቻቸው በሞቱላትና ወደነሱ ባስተላለፉዋት ሀገራቸው  የመኖር መብት ሊነፈጉ እንደማይገባና ያለ አማራጭ መኖሪያ ሜዳ ላይ መውደቅ እንደሌለባቸው አቤት ቢሉም፤ የመስተዳድሩ አካላት ወጣቶቹ ባንዲራ በመያዛቸው ቁጣቸውን በመግለጽ ያለምንም መፍትሔ መመለሳቸውን  ነዋሪዎቹ በሀዘን ተናግረዋል። በአሁኑ ሰኣት ህዝቡ የመንግስት ያለህ፣ያገር ያለህ እያለ ተማጽኖውን እያሰማ እንደሚገኝም ነዋሪዎቹ ይናገራሉ።