(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 27/2011) በአዲስ አበባ ዛሬ ከ51 ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ ማውጣት ስነ ስርዓት ተካሄደ።
እጣ ከወጣባቸው ቤቶች ውስጥም 32 ሺህ 653 ቤቶች የ20/80 ቤቶች ሲሆኑ፥ ቀሪዎቹ 18 ሺህ 576 ደግሞ የ40/60 ቤቶች ናቸው።
ቤቶቹ በኦሮሚያ ክልል ስለሚገኙ ለአዲስ አበባ ነዋሮዎች ሊሰጥ አይገባም የሚሉ ብሄርተኞች በአካባቢው አደጋ እናደርሳለኝ እያሉ እየዛቱ መሆናቸውኝ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በኢትዮጵያ ባለፉት 13 አመታት በአዲስ አበበና በመላ ሀገሪቱ ከ385 ሺህ በላይ ኮንደሚኔየም ቤቶች ተገንብተው ለተጠቃሚዎች ተላልፈዋል። የተወሰኑት ደግሞ ገና በግንባታ ላይ ናቸው።
በዚህም 1 ሚሊየን ለሚጠጉ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር እንደተቻለ ነው የሚገለጸው።
በዛሬው እለትም በአዲስ አበባ ከ51 ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ የማውጣት ስነ ስርዓት ተካሄዷል።
ከነዚሁም መካከል የ20/80 ፕሮግራም ቤቶች ውስጥ 1 ሺህ 248 ስቲዲዮ፣ 18 ሺህ 823 ባለ አንድ መኝታ፣ 7 ሺህ 127 ባለ ሁለት መኝታ እና 5 ሺህ 455 ቤቶች ደግሞ ባለ ሶስት መኝታ ናቸው።
የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ውስጥ የሚካተቱት በ1997 ዓ.ም ተመዝግበው በ2005 ዓ.ም በነባር መደብ የተመዘገቡና በ2005 ዓ.ም የአዲስ ባለ ሶስት መኝታ ተመዝጋቢዎች ናቸው ተብሏል።
በእጣ አወጣጥ ስነ ስርዓቱ ላይ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ልማት በጋራ ተጠቃሚነት ካልተመሰረተ ተጎጅና ተጠቃሚን የሚፈጥር ነው ብለዋል።
በተለይ ለቤቶች ግንባታ ሲባል ከእርሻ ቦታቸው የለቀቁ አርሶ አደሮችና የአርሶ አደር ልጆች የሁላችንም ህመም ነው ብለዋል።
በዚህም የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔና የቤቶች አሰተዳደር ቦርድ አርሶ አደሮችና የአርሶ አደር ልጆች ያለ እጣ እንዲሰጣቸው መወሰኑን ይፋ አድርገዋል።
ከንቲባው ይህን ይበሉ እንጂ የጋራ መኖሪያ የተሰራበት ቦታ አካባቢው የኦሮሚያ ክልል ነው በሚል የቤቶች መተላላፍን በመቃወም በርካታ ዘመቻዎች ተከፍተዋል።
ይሕንኑ የሚያስተጋቡ ብሄርተኞች በአካባቢው አደጋ እናደርሳልን እያሉም በአደባባይ እየዛቱ ናቸው ተብሏል።