ኢሳት (የካቲት 3 ፥ 2009)
በአዲስ አበባ ከተማ በተከሰተ ከፍተኛ የውሃ ዕጥረት አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች ለምግብ ማብሰያነት የወንዝ ውሃ እስከመጠቀም መድረሳቸው ተገለጸ። ሆቴሎችም በተከሰተው ከፍተኛ የውሃ እትረት እንግዶችን በተገቢው ላምስተናገድ መቸገራቸውም ተመልክቷል። የውሃ ዕጥረቱ ለውሃ ወለድ በሽታዎች መንስዔ ሆኗል።
በከተማዋ በጉለሌና የካ ክፍለ ከተሞች ብቻ የውሃ አቅርቦ ከተቋረጠ ከሁለት ወር በላይ መቆጠሩንና ነዋሪዎችን ለጤና ችግሮችና ለማህበራዊ ቀውሶች መዳረጋቸውን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
ተመሳሳይ ችግር በየካ ክፍለ ከተማ መኖሩን የሚናገሩት ነዋሪዎች ችግሩ ከአቅማቸው በላይ እየሆነ መምጣቱን አስታውቀዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ አዲስ ገበያ አስኮ አዲስ ሰፈር፣ አለም ባንክ ልደታ ኮንዶሚኒየም፣ ቦሌ ቡልቡላ፣ ቦሌ መድሃኒያለም የተሰኙ አካባቢዎች ችግሩ በመባባስ ላይ ካለባቸው የከተማ ስፍራዎች ዋነኞቹ መሆናቸው ተመልክቷል።
የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣናት በበኩሉ ችግሩ በከርሰ ምድር የውሃ መገናኛዎች ላይ በተፈጠረ እጥረት መሆኑን ለመንግስት መገኛኛ ብዙሃን በሰጠው ምላሽ ገልጿል።
በመዲናዋ ለአመታት በዘለቀው በዚሁ የውሃ እጥረት ከነዋሪዎች በተጨማሪ ኤምባሲዎች፣ እንዲሁም ሆቴሎችና የህክምና መስጫ ተቋማት የችግሩ ሰላባ መሆናቸው ታውቋል። ከሁለት ወር በላይ የውሃ አገልግሎትን ያጡ ነዋሪዎች በበኩላቸው ችግሩ ለተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች እንደዳረጋቸው ይናገራሉ።
በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ በርካታ ሆቴሎች እንዲሁም ለእንግዶቻቸው የተሟላ አገልግሎት መስጠት ባለመቻላቸው ከደንደንበኞቻቸው መመለስ የማይችሉት ቅሬታ እየቀረበባቸው እንደሆነና ችግሩ በገቢያቸው ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን ገልጸዋል።
የከተማዋ አስተዳደር ከአመታት በፊት ጀምሮ ችግሩን ለመቅረፍ በተደጋጋሚ ቃል ቢገባም የውሃ አቅርቦት እጥረት እየተባባሰ መምጣቱን ነዋሪዎቹና የንግዱ ተቋማት ባለቤቶች አስረድተዋል።
ባለፈው አመት ክረምት ወር በከተማዋ እየተባባሰ የመጣን የውሃ እጥረት በርካታ ሰዎች የወንዝ ውሃን ለምግብ ማብሰያና ለተለያዩ ፍላጎቶች በመጠቀማቸው የኮሌራ በሽታ ወረርሽን መከሰቱ ይታወሳል። የህክምና ባለሙያዎች በበኩላቸው ከውሃ እጥረት ጋር በተገናኘ በተለይ ህጻናት ለተለያዩ በሽታዎች እየተዳረጉ መሆኑን ገልጸዋል።