የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ከእስር የሚለቀቁበትን ሁኔታ እንዲያመቻች ተጠየቀ

ኢሳት (የካቲት 3 ፥ 2009)

የብሪታኒያ የፓርላማ አባላት የአገራቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ከእስር የሚለቀቁበትን ሁኔታ እንዲያመቻች ዳግም ጥያቄ ማቅረባቸውን የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን አርብ ዘገቡ።

የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ 62ኛ አመት የልደት በዓልን አስመልክቶ በብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር መኖሪያ ቤት አካባቢ ዝግጅትን ያካሄዱ የፓርላማ አባላትና የአቶ አንዳርጋቸው ቤተሰቦች የሃገሪቱ ባለስልጣናት ለዜጋቸው መብት መከበር ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ ማቅረባቸው ኢስሊንግተን ጋዜት የተሰኘ ጋዜጣ ዘግቧል።

በዚሁ ስነስርዓት ላይ የተገኙት የብሪታኒያ የፓርላማ አባላትና በተቃዋሚ ፓርቲ ውስጥ የውጭ ጉዳዮች የሚከታተሉት ኤሚሊ ቶርቤሪ (Emily Thornberry) የብሪታኒያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ለአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳዩ ልዩ ትኩረት እንዲሰጡ አሳስበዋል።

“ብሪታኒያ መንግስት ዜጋውን ከእስር ለማስለቀቅ በቂ ተፅዕኖና ሃይል (ጫና) አለማድረጉ ሊገባኝ ያልቻለ ጉዳይ ነው” ሲሉ የፓርላማ አባሏ ለጋዜጣው አስታውቀዋል።

አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ገና ከጅምሩ የተያዙበት ሁኔታ ህገወጥ ነው ያሉት የፓርላማ አባሏ የሃገራቸው መንግስት ዜጋውን ከእስር ለማስለቀቅ በቂ ጥረት አለማድረጉን ተችተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቦሪስ በዚሁ ጉዳይ ሊያፍሩ ይገባቸዋል በማለት ኤሚሊ ቶርንቤሪ አክለው ተናግረዋል።

የብሪታኒያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጥረታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያ የፓርላማ አባሏ ከቦሪስ ጆንሰን ጋር ውይይት ማካሄዳቸውንም ጋዜጣው በዘገባው አስነብቧል።

በዚሁ ስነስርዓት ላይ ወደ 100 የሚጠጉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በመገኘት ተመሳሳይ ጥሪን ያቀረቡ ሲሆን፣ የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ ለተነሱ ስጋቶች ትኩረት እንዲሰጡ መጠየቃቸውንም ለመረዳት ተችሏል።

የፓርላማ አባልና ተመሳሳይ ዘመቻን በማካሄድ የሚታወቁ ጀርሚ ኮርቢን (Jermy Corbyn) በበኩላቸው የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ለአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከእስር መፈታት ጥረት እንዲያደርጉ የጹሁፉ መልዕክት ማቅረባቸውን አስታውቀዋል።

የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አቶ አንዳርጋቸው የህግ አግልግሎት እንዲያገኙ ስምምነት ቢደርስም ከአንድ አመት በላይ ስምምነቱ ወደተግባር አለመለወጡ ስጋት እንዳሳደረበት ለጋዜጣው በሰጠው ምላሽ አስታውቋል።

ባለፈው አመት በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉ የሃገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት አቶ አንዳርጋቸው የህግ ምክር እንዲያገኙ ከኢትዮጵያ ጋር ስምምምነት መድረሳቸው የሚታወስ ነው።

ይሁንና የብሪታኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዚሁ ስምምነት መሰረት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ የህግ ምክር የሚያገኙበት ሁኔታ አለመመቻቸቱን ይገልጻል።

የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የተደረሰው ስምምነት በምን ሁኔታ ተግባራዊ ሊሆን እንዳልቻለ የሰጡት ምላሽ የለም።