ህዳር 18 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- ዘጋቢያችን እንደገለጠው መንግስት መድረኩ የብሶት ማሰሚያ መድረክ እንዳይሆን በመስጋት ከፍተኛ ጥረት አድርጎ ነበር። ከዚህ ቀደም ህዝቡ መስቀል አደባባይ ሲደርስ ” መለስ ሌባ፣ መለስ ይውረድ” የሚል ጩኸት በማሰማቱ፣ የመሮጫው አቅጣጫ ከአምና ጀመሮ እንዲቀዬር ተድረጎአል።
የዘንድሮው የመሮጫ አቅጣጫ ለገጽታ ግንባታ በሚል የጎተራን የማሳለጫ መንገድ እንዲያካትት ተድረጎአል። ይህም ሁሉ ጥረት ተደርጎ ህዝቡ ገዢውን ፓርቲ ከማውገዝና ብሶቱን ከማሰማት ወደ ሁዋላ አላላም።
36 ሺ ሰዎች በተሳተፉበት 11ኛው ታላቁ ሩጫ በቀጥታ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ እየተላለፈ በነበረበት ሰአት ህዝቡ “ኢህአዴግ ሌባ” ፣ የሚል ድምጽ ማሰማት በመጀመሩ ከሩጫው ሜዳ የሚመጣው ድምጽ
ተቋርጦ፣ የስቱዲዮ ድምጽ እንዲገባ ተደርጎአል።
ዘጋቢያችን በተለያዩ ቦታዎች ተዘዋውሮ እንደተመለከተው ሯጮቹ በተለያዩ ዜማዎችኢህአዴግንና መሪውን አቶ መለስ ዜናዊን አውግዘዋል ።
በእለቱ “ኢህአዴግ ሌባ፣ መንግስት ሌባ፣ ለዛሬ አመት በአዲስ መንግስት፣ ምን አለ እስክንድር ምን አለ፣ አገሬን ትቹ አልሄድም አለ፣ ምን አለ ተመስገን ምን አለ፣ አገሬን ትቼ አልሰደድም አለ፣ እባክህ ኢህአዴግ 20 ዓመት ከበቂ በላይ ነውና በቃህ ፣ ሰላም ነው እያለ መሬቱን ሸጠው. ፣ አይቀርም እንደጋዳፊ መውደቅ፣ ፍትህ ለኢትዮጵያ፣ ፌደራል ውሻ ” የሚሉ መፈክሮችና ብሶቶች ተሰምተዋል።
ተሳታፊዎቹ ሀይሌ የታፈነውን ብሶታቸውን እንዲተነፍሱ ስላስቻላቸውም ምስጋና ሲያቀርቡ ተስምተዋል።
የፌደራል ፖሊሶች ተቃውሞ ሲያሰሙ የነበሩ ሰዎችን እየያዙ ማሰራቸውም ታውቋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በእየ ሁለት ሳምንቱ የሚካሄደው የሚዩዚክ ሜይ ዴይ የምጸሀፍ ንባብና ውይይት ክበብ ህዳር 17 ቀን 2004 ዓም ከቀኑ በ8 ሰዓት ላይ 5 ኪሎ በሚገኘው ሙዚዬም አዳራሽ በነጋድራስ ገብረህይወት ባይከዳኝ ስራዎች ላይ በፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ ወረቀት አቅራቢነት ሊያደርገው የነበረውን የመጽሀፍ ግምገማ
አቋርጧል።
ውይይቱ የተሰረዘው የውይይቱ መሪ የሆነው የመንግስት ጋዜጠኛ የሆነ የኤፍ ኤም አዲስ 97.1 አዘጋጅ በፍቃዱ አባይ በታላቁ ሪጫ ላይ ፖሊስ መንግስትን ተሳድበዋል በሚል ከአሰራቸው ሰዎች መካከል አንዱ ሆኖ በመገኘቱ ነው።