በሞያሌ ከተማ በተነሳው ግጭት 7 ሰዎች ተገደሉ

ህዳር 18 ቀን 2004 /

ኢሳት ዜና:-በሞያሌ ከተማ የኦሮሞ ተወላጅ በሆኑት ቦረናዎችና የሶማሊ ተወላጅ በሆኑት ገሪዎች መካከል በተነሳ ግጭት ሰባት ሰዎች ተገድለዋል፣ ከሟቾች መካከል ሁለት ሴቶች  ይገኙበታል።

ህዳር 10 ቀን የተነሳው ግጭት ገሪዎች ወይም ሶማሊዎች በከተማው የሚገኘውን አንድ ትምህርት ቤት ለእኛ መሆን አለበት የሚል ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ ሲሆን፣ ቦረናዎች ደግሞ በእኛ መሬት ላይ ያለን ትምህርት ቤት ሶማሊዎች ሊወስዱት አይገባም ማለታቸውን ተከትሎ ነው።

በግጭቱ ከገሪዎች በኩል አምስት ሰዎች ሲገደሉ፣ ከቦረና በኩል ደግሞ ሁለት ሰዎች ተገድለዋል። ግጭቱ እንደተፈጠረ የፌደራል ፖሊስ በአካባቢው ተገኝቶ ለማረጋጋት ቢሞክርም ውጥረቱ ግን አሁንም እንዳለ ነው።

የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት የግጭቱ መንስኤ የመንግስት የጎሳ ፖሊሲ የፈጠረው ነው።

የብሄረሰቦችን ቀን ለማክበር ደፋ ቀና የሚለው ኢህአዴግ ፣  ፖሊሲው ስራ ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ የጎሳ ግጭቶች ተከስተዋል።

በቦረና የተፈጠረው ችግርም ለዘመናት በአንድነት የኖሩት ህዝቦችን ለመከፋፈል የተደረገው ሙከራ ውጤት መሆኑን ሌላው የአካባቢው ነዋሪ አቶ በቀለ ጉርሱም ያስረዳሉ።

ኢህአዴግ መራሹ መንግስት የብሄር ብሄረሰቦችን ችግር እፈታለሁ በሚል ሰበብ፣ አገሪቱን በጎሳ መሸንሸኑ ኢትዮጵያን የሚከፋፍልና አገሪቱን በማያባራ የጎሳ ግጭት  ውስጥ የሚከት ነው በማለት ምሁራን
እንደሚነቅፉ ይታወቃል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ጋብቻ ለመፈጸም ሳይቀር የብሄር ማንነት መጠየቅ መጀመሩ ብዙዎችን ያሳሰበ ጉዳይ ሆኗል።